Thursday, October 31, 2013

የስደት መንስኤ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ እያለ መንግስት ግን ችግሩን ወደ ደላላ 
መንግስት ስደትን ለመቆጣጠር በሚል ለደላላዎች አዋጅ እንዳወጣው ሁሉ ለአገራችን ምስቅልቅልና የስደት ምንጭ ደላላ የሆነው ራሱን የሚገድብ አዋጅ ያስፈልገዋል፡፡ ስልጣን በአዋጅ (በህግ) እስካልተገደበና መረን እስካልያዘ ድረስ ኢትዮጵያውያን ይሰደዳሉ፡፡ ካድሬዎችም ቢሆን!
ስደትን በጊዜያዊ አዋጅ?

ኢትዮጵያዊያን በግል ሳይሆን በመንጋ የተወለዱበትን ቀዬ ትተው ወደማያውቁት ምድር እየጎረፉ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ካሰቡት ሳይደርሱ በየ በርሃውና ባህሩ እየቀሩ ነው፡፡ ይህን የኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰፊው መዘገባቸውን ተከትሎ መንግስትም ‹‹መፍትሄ›› የሚለውን አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱት በአመለካከት ችግር መሆኑን የሚያምነው መንግስት በጊዜያዊ አዋጅ ስደትን ለመከላከል እየሞከረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የገዥዎች እንጅ የዜጎቿ ሆና አታውቅም፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ደግሞ ይህ ባይተዋርነት ሌላ መልክን ይዟል፡፡ ተራ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሙዚቀኞች፣ ጀኔራሎችም እግሬን አውጭኝ ብለው ከአገር እየተሰደዱ ነው፡፡ መንግስት ይህኛውን ሳይሆን በሱዳን፣ ኬንያና ሶማሊያ የሚፈልሱትን ነው ለማቆም እጥራለሁ የሚለን፡፡ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጀኔራሎች የሚሰደዱበትን አብሮ ማንሳት ፖለቲካዊ ቃና ስለሚይዝ ማንሳት አልፈለገም፡፡ 
እርግጥ ነው ወንድምና እህቶቻችን ኮንተይነር ውስጥ መሞታቸው ልብ የሚነካ ነው፡፡ የአሳ ራት፣ የበርሃ ሲሳይ ሲሆኑም እጅጉን ያስቆጫል፡፡ በማያውቁት አገር ፖሊስ ሲገረፉ፣ ሲደፈሩና ሲንገላቱ መስማት ያሳምማል፡፡ መፍትሄም ያስፈልገዋል፡፡ ግን ግን ማዕከላዊ (የኢትዮጵያዊ ጓንታናሞ)፣ የቀጨኔው ወረዳ ዘጠኝ፣ ዝዋይ ታጉረው የሚገረፉት፣ የሚሰቃዩት ዜጎች በስደት ከሚሰቃዩት በምን ይሻላሉ? ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ተቃዋሚ፣አክራሪ…… እየተባሉ የሚገረፉት፣ ከስራ የሚባረሩት የተወለዱበትን አገር ጥለው ሲጠፉ ተጠያቂው ማን ነው? ለምን ለዚህኛው ባይተዋርነትስ አወጅ አይወጣለትም?

የአገራችን ዋነኛው የስደት መንስኤ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ እያለ መንግስት ግን ችግሩን ወደ ደላላ ዝቅ አድርጎታል፡፡ እውነቱን ለመናገር ለኢትዮጵያውያን የስደት ስቃይ መጠየቅ ካለበት ለፖለቲካ ምስቅልቅሉ መንስኤ የሆነው መንግስት ራሱ ነው፡፡

እውቅ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጀኔራሎች ወደ ውጭ የሚሰደዱት የቀን ስራ ለመስራት ሳይሆን ልክ ወደ አረብ አገር የሚሰደዴት እህቶቻችን የመን ላይ እንደሚገጥማቸው እስራትና ግርፋት እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ስቃዩ ስለበዛባቸው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች የዚህ ስቃይ ሰለባዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች መውጫ ቀዳዳውን ካገኙ አሁንም ይሰደዳሉ፡፡ ለአንድ ማህበረሰብ ቁልፍ የሆኑት ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ሙዚቀኞች… በፖለቲካ ችግር ከተሰደዱ ተራው ዜጋም የትውልድ አገሩን የነጠቁትን ሽሽት መጉረፉን ይቀጥላል፡፡ እኛ አገርም እየሆነ የሚገኘው ይኸው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment