የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ በላምፔዱሳ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን ዘክሮ ዋለ
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ በቅርቡ በላምፔዱሳ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በኦክቶበር 20፥2013 የሻማ ማብራት ፕርግራም በማዘጋጀት ዝክሮ ዋለ፥፥ በዝግጅቱ ላይ ከተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች፥ ሲቪክ ማህበራት እና የተለያዩ አክቲቪስቶች የስደት መንስኤውንና መፍትሄውን በዝርዝር በእለቱ ለተገኙት ታዳሚዎች መልክት አስተላልፈዋል፥፥
ዝግጅቱን የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዎይ ሊቀመንበር አቶ ፋሲል አለባቸው በለቱ የተገኙትን ታዳሚዎች የተደረገውን ጥሪ አክብረው በመምጣታቸው ያላቸውን ምስጋና በራሳቸውን በማህበሩ ስም ካቀረቡ በኋላ የስደትን ህይዎት አስከፊነትና የታሰበለት ቦታ ለመድረስ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነና በከፋ መልኩም ህይወትን እስከማጣት እንደሚያደርስ ከገለፁ በኋላ በቅርቡ በላምፔዱሳ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች እግዚአብሄር ነፍሳቸውን እንዲምርና ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ተመኝተዋል፥፥
በመቀጠልም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በተክርስቲያን ቀሲስ ካሳዬ ስደት እና አስከፊነቱን በተመለከተ አጠር ያለ መንፈሳዊ መልክት ያስተላለፉ ሲሆን እንዲሁም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ አቶ አያሌው ይመር አጠር ያለ መንፈሳዊ ገለፃ ካደረጉ በኋላ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘውን የመናገር፥ የመፃፍ እና የመደራጀት መብት የመረጠውን ሃይማኖት በሚፈልጋቸው የሃይማኖት መሪዎች እንዳይመራ አምባገነኑ የወያኔ ስርአት በመንፈጉ የኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያን ወገኖች ስደትን እንደ አማራጭ መፍትሄ በመውሰድ በየበረሃውና በየባህሩ ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል፥፥ ለዚህም ሁሉ በዜጎች ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ዘረኛው የወያኔ ስርአት ተጠያቂ እንደሚሆንና በቅርቡ የሚታዩ ምልክቶች ልክ እንደማንኛውም አምባገነን ስርአት የወያኔ ስርአትም እንደሚገረሰስና የኢትዮጵያ ህዝብም የነፃነትን ድል እንደሚቀናጅ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፥፥ ከዚያም በመቀጠል ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ወ/ሮ ሰዋሰው እና ባለቤታቸው ሚስተር ያን ኦገ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ከገለፁ በኋላ ከታዳሚው ጋር በህብረት አጭር የፀሎት ስነስረአት አድርገዋል፥፥
የተለያዩ ፖሊቲካል አክቲቪስቶች ስደት የሚፈጠረው በአንድ ሃገር የአስተዳደር ብልሹነት፥ እንደዜጋ አለመቆጠር፥ የመናገር፥ የመፃፍና የመደራጀት መበቶች ከመነፈግም አልፎ የአንድ ዘር የበላይነት በሃገሪቷ ላይ ስለሰፈነ ዜጎች ስደትን እንደአማራጭ ይወስዳሉ፥ ሆኖም ግን ስደት አማራጭ ይሁን እንጂ ለስደት መንስዔ የሆነው የወያኔ ስርአት የሚወገድበትን መንገድ ባንድነት ተባብሮ መስራት ሲቻል እንደሆነ አስገንዝበው ለዚህም አማራጩ መደራጀትና ባሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር እየተደረገ ያለውን ከሰላማዊ ትግል አንስቶ እስከ ትጥቅ ትግል የሚያረጉ ሃይሎችን መደገፋና ትግሉን በመቀላቀል እንደሆነ አስገንዝበዋል፥፥
በየፕሮግራሙ መሃል ላይ አርቲት እንዳለ ጌታነህ ያቀረበው ወቅታዊ የሆነ መዝሙርና ስነ ግጥም በለቱ የተገኙትን ታዳሚዎች በእንባ ሲያራጭ አምሽቷል፥፥
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ ይህን የሻማ ማብራት ፕሮግራም ላዘጋጁትና ዝግጅቱም የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፆ ላረጉት ለአቶ ዳንኤል አምዶም ፥ ለወ/ት ሳራ ግርማ፥ ወ/ት ለምለም አንዳርጌ፥ አቶ ዮናስ ታምሩ፥ አቶ ሚሊዮን ሊማ፥ አቶ ጌታቸው አበበ፥ እና አቶ ሃሰን ሞሃመድ ታላቅ ምስጋና ያቀርባል፥፥
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ
ኦክቶበር 22፥2013
No comments:
Post a Comment