Thursday, April 11, 2013

የተፈናቀሉ አማሮች ተመለሱ ተባሉ፣ “ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ”

ሕግ አለማወቅ በሕግ ከመጠየቅ የማያድን ከሆነ ሕግ እያወቀ ያጠፋውስ ላይ ቅጣቱ እንዴት አይከብድ?

Gudayachn Blog
ጌታቸው በቀለ፣ ኦስሎ
ባለፈው ጊዜ በፈስቡክ ገፄ ላይ ” ‘ሪፖርተር ጋዜጣ’ ስለ ቤንሻንጉል መፈናቀል አልስማም ይሆንን? ዜናው አዲስ አበባ አልደረሰ ይሆን?” እያልኩ ስጨነቅ ሪፖርተር በዛሬው ሮብ ሚያዝያ 2/2005 እትሙ የቤንሻንጉል ተፈናቃዮችን “በቃ ተዉት ኑ ተብሏል” የሚል መሰል ዜና አስነብቧል። እኔ ደግሞ የእራት መብያ ሰአቴን ግማሹን ለኢቲቪ ቀሪውን ለኢሣት አድርጌ መንግስት ስለጉዳዩ መግለጫ ይሰጣል ብዬ መጠበቄ ቆጨኝ።
ምክንያቱም ኢቲቪም ፈርቶ ይሁን አፍሮ አይታወቅም ምንም አላለም። በ1997 ዓ.ም “ድምፄ ተነጠቀ” ብሎ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለተቃውሞ ሲወጣ መንግስት መጀመርያ ያደረገው ጉዳዩ ብሔራዊ ጉዳይ ላለማስመሰል ለፀጥታው ችግር (በከተማዋ ከንቲባ ደረጃ ያለ ችግር ይመስል) በየሰዓቱ ዜና የሚያነቡት ኤፌም ራድዮኖች አቶ አርከበን ብቻ እንዲጠይቁ ተደረጉ። ሰዓቱ እይረፈደ ሲመጣ መስርያቤቶች መዘጋታቸው ታወቀ። ከምሳ በኃላ “ምነው እንትና” አለ እና የፈድራል ፖሊስ መግለጫውን ገባበት።
አሁንም ቤንሻንጉል “ሂዱ! ውጡ!” ብሎ በሺ የሚቆጠር ሕዝብ በስለት፣ በጥይት ወዘተ እየተሳደደ፣ አራስ መንገድ ላይ እየወለደች፣ ሕፃናት ትምህርታቸውን ጥለው ከወላጆቻቸው ተለያይተው በየጫካው ውስጥ ሲንከራተቱ፣ አብያተ ክርስታያናት ተዘግተው ካህናት ቁልፍ አምጡ ተብለው ሲደበደቡ እና ሲታሰሩ ያልሰማው መንግስት ዛሬ ቤንሻንጉል ክልል ስም “ኑ ተብሏል” ብሎ መናገሩ እና በመኪና እየጫነ በግድ መውሰድ መጀመሩ ተሰምቷል። አንዳንዶች ወዴት እንደሚወሰዱ ገና አልታወቀም እያሉ መሆኑ ሳይዘነጋ። ለነገሩ ዛሬ ተፈናቃዮቹ የተቃውሞ ሰልፍ ሊያደርጉ የነበረ መሆኑ እና የአለም አቀፍ የኢትዮጵያን ቁጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማየሉ ሁኔታውን ቶሎ የማድበስበስ ሥራ ለመስራት መንግስት እንዲያስብ ሳያደርገው አልቀረም። ስለዚህም “ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ” የሚለውን አባባል መንግስት ሥራ ላይ ለማዋል የተገደደ መስሏል። ይሄውም የህዝብ ሃሳብ በሌላ ነገር ሲጠመድ ሰይጣናዊ ሥራ መስራት ሕዝብ በአንድላይ ሲቆጣ ከነገር አለሙ መለስ ማለት።
በእጅም ሆነ በማንኪያ ይህ ሁሉ የመንግስት ተግባር የሚያመለክተው አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው። ኢትዮጵያ “መከፋፈሏን” ያወቀ የተረዳ ግን ይህንን የሚያበረታታ መንግስት እንዳለን። ለእዚህም ከሰሞኑ ክስተት በተጨማሪ ያለፉት ሁለት ወራትን ሶስት ክስተቶች መመልከት ይቻላል። እነርሱም፣
- ባለፈው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎች “የኦሮሞ ተወላጅ በመሆናችን ብቻ ተቃዋሚ ናችሁ ተብለን ካለትራንስክሪፕት ተባረርን በየቱቦው ውስጥ ነው ይምንተኛው” ማለታቸው ጆሮ ዳባ ልበስ መባላቸው፣
- ጅጅጋ ዛሬ የሱማሌ ክፍል ነች ወይስ የኢትዮጵያ? እስኪባል ድረስ እስካሁን ከየት እንደመጡ በማይታወቁ የሚሊሻ ኃይል ስትተዳደር እና ማንኛውም አማርኛ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን የጉራግኛ ትግርኛ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሳይቀር እየተሳቀቀ የሚኖርባት መሆኗ እንድያውም የአማርኛ ተናጋሪዎች ከግማሽ ክፍለ-ዘመን በላይ የኖሩበትን የግል ቤት ካለምንም ካሳ መነጠቃቸው እና
- ዜጋ በሀገሩ ላይ ለፋሺሽቱ ግራዝያኒ የተሰራውን ሃውልት መቃወም ኢህአዴግን መቃወም የሆነበት እና ህዝቡ በታክሲ ውስጥ ሳይቀር የግራዝያኒን ሃውልት ተቃውሞ መናገር የፈራበት ሁኔታ በቂ ማስረጃዎች ናቸው።
ለእዚህ ሁሉ ግን መልሱን ልብ አላለው ካልሆነ በስተቀር “ሪፖርተር ጋዜጣ” እራሱ የመለሰው ይመስለኛል። በጋዜጣው ፀሐፊ ጌታሁን ወርቁ በመጋቢት 29/2005 የተፃፈው
“ሕግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም” በሚል አርዕስት ስር እንዲህ የሚል ይገኝበታል።
ይህ አነጋገር (Maxim) በሕግ ሙያ ከተለመዱት መርሆች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡ በሁሉም የሕግ ሥርዓት ውስጥ ለዘመናት ታውቆ የኖረ፣ የሚፈጸምም ነው፡፡ በሕግ ሙያ ከተለመዱ ጽንሰ ሐሳቦች ውስጥ በብዛት በኅበረተሰቡ ውስጥ የሚታወቅም መርህ ነው፡፡ ትርጉሙ ግልጽ ነው፡፡
አንድ ሰው ሕጉን ሳያውቅ በፈጸመው ጥሰት ተጠያቂነቱ አይቀርለትም፡፡ ጥፋት ያጠፋ ሰው ‹‹ሕጉን አላውቀውም›› ብሎ ሊከላከል አይችልም ማለት ነው፡፡ ጋሪ ስላፐር የተባለ እንግሊዛዊ የሕግ ባለሙያ፣ መርሁን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ሕግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም›› ማለት፣ ‹‹ለምሳሌ አንተ ከአንድ ሰው ጋር የነበረህን የውል ግዴታ ሳታከብር ስትቀር ወይም የመንጃ ፈቃድ ሳይኖርህ መኪና ስትነዳ፣ የሠራኸው ሥራ በሕግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ባታውቅም ክስ ይመሠረትብሃል፤ በወንጀል ከሆነ ደግሞ በዓቃቤ ሕግ ትከሰሳለህ ማለት ነው፡፡›› በዚህ መርህ መሠረት በአገሪቱ የወጡትን ሕግጋት በሙሉ፣ ዜጎች ወይም በአገሪቱ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ያውቁታል ተብሎ ግምት ይወሰዳል፡፡
….ከዚህ በላይ በጽንሰ ሐሳብ ትንታኔው የተገለጸው ከሞላ ጎደል በአገራችንም ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ሕጉ ማንኛውም ዜጋ/አገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የኢትዮጵያን ሕግጋትን ያውቃል የሚል ግምት ይወስዳል፡፡ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 3/1987 በአንቀጽ 3 ‹‹ማናቸውም የፌዴራል ወይም የክልል ሕግ አውጭ፣ አስፈጻሚ እና ተርጓሚ እንዲሁም ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል፣ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣ ሕግን የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል፤›› በማለት ሕግን ማወቅና መቀበል በግዴታ መልክ አስቀምጧል፡፡ ይህን የመቀበል ድንጋጌ በመተላለፍ ሕጉን አለማወቅም ሆነ አለመቀበል በማያውቀው/ባልተቀበለው ሰው ላይ ያለውን ተፈጻሚነት አያስቀረውም፡፡ ስለዚህ ማንኛውም በነጋሪት ጋዜጣ የወጣን ሕግ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ያውቃል፣ ተቀብሎታል የሚል የሕግ ግምት መኖሩን ልብ ማለት ይገባል፡፡
ከዚህ ሌላ በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል ‹‹ሕግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም›› የሚለው መርህ ተካትቶ እናገኛለን፡፡ መርሁ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ‹‹ከውል ውጭ ኃላፊነት›› በሚለው ክፍል የሚገኝ ነው፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2035 ‹‹አንድ ሰው በሕግ ላይ በትክክል ተገልጾ የተመለከተውን ልዩ ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና፣ ሥርዓት የጣሰ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው›› በማለት በንዑስ ቁጥር አንድ ደንግጓል፡፡ በንዑስ ቁጥር ሁለት ደግሞ ‹‹ሕግን አለማወቅ ይቅርታ ሊያስገኝ አይችልም›› በማለት መርሁን ያለምንም ልዩ ሁኔታ ደንግጓል፡፡
ይላል።
አሁን ባለው የሀገሪቱ ሕግ “ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ግለሰብ በፈቀደበት ቦታ የመኖር እና ሀብት የማፍራት ሙሉ መብት አለው” ይላል።እናም በሀገራችን የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ሃገርን ከጥፋት ህዝብን ከስደት ያድናል። “ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ” ግን ለሀገሪቱ ችግር መፍትሄ አይሆንም። ሕግ አለማወቅ በሕግ ከመጠየቅ የማያድን ከሆነ ሕግ እያወቀ ያጠፋውስ ላይ ቅጣቱ እንዴት አይከብድ?
አበቃሁ።

No comments:

Post a Comment