Wednesday, April 3, 2013


መንግስት አቀባባይ የሆነበት የእህቶቻችን ስቃይ

"እኛን ማገዝ ግድ ነው" ዶ/ር ማይገነት
ethiopian girl in arabia
“በግል ጥሪ የላከልኝ የለም። ያገባኛል የምትሉ እንድትገኙ የሚል መልዕክት ሰማሁና መጣሁ። የማውቀውንና ያየሁትን እውነት ተናገርኩ። ስቃዩ ከሚነገረው በላይ ነው። የሚነገረውና በተግባር የሚደርሰው በእጅጉ የተለያየ ነው …” በማለት ምስክርነቷን ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ለጀመሩት ወገኖች ማካፈሏን የምትናገረው ወ/ት ዘቢባ ዘለቀ ናት። በንግግሯ ሁሉ መፍትሔ አንዲፈለግ አበክራ ትጠይቃለች።
በቡድን ተደፍረው፣ በመከራ አልፈው፣ በስልክ የሚጠየቀው ተከፍሎላቸው ጂዳና ሪያድ የሚገቡትን እህቶች አግኝታ አነጋግራለች። በቡድን የተደፈሩት እህቶች መንፈሳቸው የተሰበረ ነው። በፍጹም ስነ ልቦናቸው የሚያገግም አይመስልም። ጭው ባለ በረሃ መጫወቻ ሆነው ያሰቡበት ደርሰው ያገኘቻቸው የሚነገራቸውና የሚያጋጥማቸው ፈጽሞ የተለያየ እንደሆነ ለጎልጉል በስልክ አስታውቃለች።
በህጋዊ መንገድ በኤጀንሲ ካገር ከሚወጡት መካከል ድብደባና መከራ የሚገጥማቸው መኖራቸውን፣ ይህ የተለመደ እንደሆነ የጠቀሰችው ወ/ት ዘቢባ “ወገኖቻችን አንዴ ካገር ከወጡ አስተዋሽ ስለሌላቸው እየተገደሉ ነው። ማጣራትና መመርመር ቢቻል ብዙ ጉድ አለው። ወገኖቻችን አልቀዋል። እያለቁ ነው” ብላለች።
ጂቡቲ ደርሰው ወደ የመን የሚያደርጉት ጉዞና የመን ከደረሱ በኋላ የሚያጋጥማቸው መከራ በቃላት የሚገለጽ እንዳልሆነ ያመለከተችው ዘቢባ፣ በየመን ያለው ችግር በወንድሞች ላይም በእኩል ደረጃ ይፈጸማል ብላለች። ከየመን ወደ ወደ ሳዑዲ ለመግባት በእግርና በመኪና በሚደረገው ጉዞ ያለው ፈተና እጅግ ዘግናኝ መሆኑንን በመግለጽ ይህ ሰቆቃ ሊያበቃ የሚችልበትን መንግድ መፈለግ እንደሚያሻ ተናግራለች። ለዚሁም የአቅሟን ለማበርከት የኢትዮጵያ የሴቶች መብት ማዕከል ስብሰባ መገኘቷን አመልክታለች።

No comments:

Post a Comment