ባለፈው ስለ የመኾኒ ኗሪዎች መኖርያ ቤት ‘ኢ-ሕጋዊ’ መባሉና እንዲፈርስ መወሰኑ ፅፌ ነበር። ነዋሪዎቹ የራሳቸው መኖርያ ቤት እንዲያፈርሱ እስከሚቀጥለው ዓርብ (ነገ መጋቢት 27፣ 2005 ዓም) የመጨረሻ ቀነ ገደብ (dead line) እንደተሰጣቸው ተገልፆ ነበር።
ይህን የተነገራቸው የመኾኒ ነዋሪዎች ለመንግስት ኣካላት ኣማራጭ መጠልያ እንዲሰጣቸው ኣቤት ሲሉ የከረሙ ሲሆን ባለፈው ሦስት ቀናት እግዚኣብሄር/ ኣላህ እንዲረዳቸው ተሰባስበው ሲፀልዩ ነበር። ፀሎታቸው እስከ ዓርብ (ቤታቸው የሚፈርስበት ቀን) እንደሚቀጥሉ ተስማምተው ዓርብ (ቤታቸው በሃይል ሲፈርስ) ግን ተቃውሞ ለማሰማት ተዘጋጅተው ነበር።
ይህንን ዉሳኔ ያወቁና (ተቃውሞውን ያሰጋቸው) የመንግስት ኣካላት መኖርያ ቤቶቹ ከሚፈርሱበት ቀነ ገደብ ሁለት ቀናት ቀድመው ትናንት ሮብ (መጋቢት 25) ሃይል በተሞላበት በግፍ ቤቶችን ኣፍርሰዋል። በትናንትናው ዕለት የፈረሱ ቤቶች በመንግስት ኣካላት 700 መሆናቸው ሲነገር ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግን ከ2000 በላይ መኖርያ ቤቶች በመንግስት ምልሻዎች ፈርሰዋል። በመጀመርያው ዙር ከ1300-1500 ቤቶች እንደሚፈርሱ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የፈረሱ ግን ከ2000 በላይ መሆናቸው ሁኔታው ኣሳሳቢ ሁነዋል ።
መኖርያ ቤቶቹ ሲፈርሱ በሃይል ከመሆኑ ተያይዞ ከነ ንብረቶቻቸው እየወደሙ ነው። ኗሪዎቹ ያላቸው ተቃውሞ ለማሰማት የቤት ንብረታቸው ከሚፈርሰው ቤት ለማስወጣት ኣለመቻላቸው ሁኔታው ኣሳዛኝ ያደርገዋል። በዚህ መሰረት የኣንድ በርበሬ ነጋዴ 80 ኲንታል በላይ በርበሬ የያዘ ቤት በመፍረሱ ከጥቅም ዉጭ ሁነዋል።
ከዓመታት በፊት በመቐለ ከተማ ‘ገፊሕ ገረብ’ ተብሎ በሚታወቅ መንደር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ በሃይል ቤቶች ሲፈርሱ ብዙ ሰዎች በፀጥታ ኣካላት መደብደባቸው፣ መታሰራቸው፣ የተወሰኑ ደግሞ መገደላቸው ይታወቃል። በመኾኒም ተመሳሳይ ቢሆንም ከመቐለው የከፋ የሚያደርገው ኣንድ ነገር ኣለ። የደረሰኝ መረጃ ትክክል ከሆነ የከተማው 95 በመቶ እየፈረሰ ነው (ወይ ይፈርሳል)። ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ታድያ የት ይገባሉ? ሊከራዩት የሚችሉበት ቤትም እኮ የለም። እነዚህ ሰዎች ምን ሊዉጣቸው ነው? (በመቐለ እንኳ ሌላ ቤት መከራየት ይቻል ይሆናል፤ መኾኒ ግን ….!)
በከተማው የቤቶቹን መፍረስ የተቃወሙ ሰዎች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ የሞቱም ኣሉ። ከሟቾቹ ኣንዱ ‘ቤቴን እንዲፈርስ ኣልፈቅድም፣ ሌላ መግብያ የለኝም’ በማለት ከቤቱ መውጣት ስላልቻለ እዛው ቤቱ ዉስጥ እያለ ስላፈረሱት ህይወቱ ማለፉ ተሰምተዋል (ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ወደ ማይጨው ሆስፒታል ቢወሰድም ሊድን ኣልቻለም)። ሌሎች ሁለት የሞቱ እንዳሉም እየተሰማ ነው።
በኣሁኑ ሰዓት የመኾኒ ከተማ በተፈፀመባት ግፍ ምክንያት በሓዘን ተውጣ ትገኛለች። ሰሙኑ በመኾኒ ከተማ ዝናብ ከጣለ የከፋውን ኪሳራ ይደርሳል፣ ቤቶቹ ፈርሰዋል ህዝቡም መጠልያ የለውም። የግል ሚድያዎች የመኾኒ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡት ኗሪዎቹ ጥሪያቸውን ኣስተላልፈዋል። እኛም በፀሎትም (ሌላ ማድረግ ስለማንችል) ቢሆን እናስባቸው።
No comments:
Post a Comment