Tuesday, March 19, 2013


ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን ቀጥለዋል፣ በትናንትናው እለትም ድምጻቸውን አጠንክረው ሲያሰሙ ዋሉ

ለአንድ አመት ከአድን ወር በላይ ህዝብን ባስደነቀ ስርአት መብታችን ይከበር በማለት የመብት ማስከበር ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙት ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ይህኑ በጽናት የጀመሩትን ተቃውሞ በመቀጠል በትናንትናው እለት ድምጻቸውን ሲያሰሙ መዋላቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ሪፖርት ገለጸ። የሙስሊሞቹ የተቃውሞ ድምጽ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ጭምር እንደነበርም የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት የሙስሊም ኢትዮጵያዊያኑ ተቃውሞ በሻሸመኔ፣ አርሲ፣ ደሴ ፣ ስልጤ እና ሌሎችን ከተሞች ያካተተ እንደነበር ታውቋል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን አሁንም በማቅረብ ላይ ያሉት ጥያቄ ግልጽና በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ፣ አመራሮች ይፈቱ፣ አገዛዙ ለጥያቄያቸን መልስ ይስጠን የሚሉ እንደነበሩ ታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአገር ቤት የሚደረገውን ተቃውሞ በመደገፍ በትናንትናው እለት በስዊድን የሚገኙ ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በጋራ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ታውቋል።
በትናንትናው እለት በስቶክሆልም ከተማ በኢትዮጵያ ቆንስላ ፊት ለፊት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ፣ አፋኙ የወያኔ አገዛዝ ለዘመናት ተከባብሮ የኖረውን ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን በማጋጨት አገሪቱን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሩጫ በጽኑ አውግዘዋል።
በእለቱ “ሁላችንም አቡበክር ነን፣ ሁላችንም ያሲን ኑሩ ነን፣ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ፣ በጅሀዳዊ ሀረካት ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ማጋጨት አይቻልም” የሚሉ መፈክሮች መቅረባቸውን ተያይዞ የደረሰን ዘግባ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment