Tuesday, March 19, 2013


30 000 ኢትዮጵያውያንን ለጨፈጨፈው ለግራዚያኒ የተሠራውን ኃውልት መቃወም ያስከብራል!

ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ
4002 Blacksmith Drive, Garland, TX 75044, USA
መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ/ም
መግለጫMaps
በኢጣልያ፤ ከሮማ ወደ ምሥራቅ ደቡብ በምትገኝ፤ አፊሌ በምትሰኝ ትንሽ ከተማ፤ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” ለተሰኘው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ ነሐሴ 4 ቀን 2004 ዓ/ም የቫቲካን ተወካይRodolfo Graziani Fascist criminal በተገኙበት የተመረቀለትን የክብር መታሰቢያና መናፈሻ በመቃወም፤ እስከ የኢጣልያ ኤምባሲ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ ለማከናወን መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ/ም ስድስት ኪሎ የተሰበሰቡትን 43 ሰዎች፤ ዶር. ያዕቆብ ኃይለማርያምን ጭምር፤ ፖሊስ አፍሶ ማሰሩና በማግስቱ፤ መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ/ም መልቀቁ ታውቋል።
አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን፤ ከነዚሁ ውስጥ በሶስት ቀኖች ብቻ፤ በአዲስ አበባ ከተማ 30፣000 ሕዝብ ላስጨፈጨፈው፤ እነአቡነ ጴጥሮስን፤ የደብረ ሊባኖስን መነኮሳትና ሌሎችንም በጭካኔ ለረፈረፈ፤ እንዲሁም 2000 ቤተክርስቲያኖችንንና 525፣000 ቤቶችን ላስወደመው፤ በተጨማሪም በብዙ አይሮፕላኖች ባስነሰነሰው የመርዝ ጋዝ ብዙ ሕዝብ ከመግደሉ በላይ እጅግ የከፋ የአካባቢ ብክለትና 14 ሚሊዮን እንስሶችን ላወደመው የጦር ወንጀለኛ፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ የተሠራውን መታሰቢያ መቃወም ለሐገር የሚያኮራና የሚያስመሰግን እንጂ የሚያሳስር አይደለም።
እንደሚታወቀው፤ ለዚህ ዓመት የየካቲት 12 ክብረ-በዓል፤ የፋሺሽቶችን የጦር ወንጀልና የግራዚያኒን መታሰቢያ በመቃወም በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ 30 ከተሞች፤ ማለት፤ ሮማ፤ ኒውዮርክ፤ ዋሺንግተን ዲ.ሲ.፤ አትላንታ፤ ቴል አቪቭ፤ ወዘተ. የሚገኙ የብዙ ሐገሮች ዜጎች፤ ኢጣልያውያን ጭምር፤ ሰላማዊ ሰልፎች፤ ስብሰባዎች፤ ጸሎቶች አከናውነዋል። አዲስ አበባም የከተማው አስተዳደርና የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር በእለቱ ለክብረ-በዓሉ መታሰቢያ ማከናወናቸው ታውቋል።
ስለዚህ፤ በኢጣልያ ለጦር ወንጀለኛው ለግራዚያኒ መታሰቢያ እስከ መሥራት የደረሰ የፋሺሽት መንሰራራት ሊያሳስበንና ሊያስቆጨን የሚገባው፤ ዋናዎቹ የግፉ ተበዳዮች የሆንነው እኛ ኢትዮጵያውያን በመሆናችን፤ ሐገራችን አሁንም እየጠበቀች ያለችውን ፍትሕ እንድታገኝ በሰላማዊ ሰልፍ ለኢጣልያ መንግሥት ማስገንዘብ የሚደገፍ እንጂ የሚያሳስር መሆን የለበትም።
በመጨረሻም፤ ኢትዮጵያ ለተፈጸመባት እጅግ መራርና ከባድ ግፍ እስካሁን ድረስ ተገቢውን ፍትሕ ስላላገኘች፤ ድርጅታችን ለሚከተሉት ዓላማዎች እየተንቀሳቀሰ ነው፤
(ሀ) የኢጣልያ መንግሥት፤ የጦር ወንጀለኛውን የግራዚያንን መታሰቢያ እንዲያስወግድ፤
(ለ) በቫቲካንና በኢጣልያ መንግሥቶች ይዞታ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንብረቶች እንዲመለሱ፤
(ሐ) የኢጣልያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል፤
(መ) ቫቲካን፤ ከፋሺሽት ኢጣልያ ጋር ተባብራ በተፈጸመው ወንጀል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
(ሠ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር ወንጀሉን እንዲመዘግብ ነው።
ሐገራችን ላይ ለተፈጸመው የጦር ግፍ በሰብአዊ መብት መከበር የሚያምን ሁሉ በሚያከናውነው የተባበረና የጠነከረ ጥረት ተገቢው ፍትሕ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment