Sunday, May 12, 2013


ሕዝባችን ብሶቱን በሰልፍ ጭምር ለመግለጥ መነሳሳቱን እንደግፋለን!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
Ethiopian People’s Congress for United Struggle (Shengo)
ግንቦት 3፣ 2005
ሕወኃት/ኢሕአዴግ አገራችን ላይ የጫነው በአንድ ጠባብ ቡድን የበላይነትና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተው አገዛዝ የሕዝባችንን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን  ተዘርዝሮ የማያልቅ ጥፋት ላለፉት ሁለት ዓሥርት ዓመታት ሲያካሂድ መቆየቱ ማንኛውንም ለዕውነትና ለፍትህ የቆመን ዜጋ ሁሉ ያሳዘነ ነው። ይህ ሥልጣኑን ለማራዘም ማንኛውንም ዕኩይ ተግባር ከመፈፀም ወደ ኋላ የማይል አምባገነን ቡድን እስከ ዛሬ ድረስ የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ከሚጥል ክህደት ጀምሮ እስከ ተራ የአጭበርባሪነት ወንጀል በየጊዜው ሲያከናውን እንደቆየ የማያውቁ ዜጎች ይኖራሉ ብሎ ማመን ያስቸግራል።Ethiopian People's Congress for United Struggle (Congress)
ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ ደግሞ በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ ማንኛውንም ዓይነት ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ ለማፈንና ከራሱ ቁጥጥር ውጭ ሌላ የፖለቲካ፣ የሲቪክ፣ የማህበራዊም ሆነ የግለሰብ ራስን የመግለፅና የመቃወም መብቶችን ለማፈን የራሱን ሕገ መንግሥት ተብዬውን እንኳን የሚጥሱ ሕጎችን በማውጣት ከዚህ በፊት ከሕግ ውጭ ሲያካሂድ የነበረውን አፈና የሕጋዊ ከለላ በመስጠት ዜጎችን በይፋ በራሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ፍርድ ቤት ተባባሪነትና መሣሪያነት እያሰቃየና እያፈነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት አገዛዙ የሚያካሂደው አፈናና ግፍ ሞልቶ እየፈሰሰ በሁሉም ፈርጅ ዜጎችን እያማረረና ብሶቱም ከሚችለው በላይ ታፍኖ የሚገኝበት ደርጃ ላይ ደርሷል፤ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፤
  • ለሙያቸው ለዕውነት የቆሙ ጋዜጠኞችና በሕጋዊነት በተመዘገቡ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራር አባላትን በሽብርተኝነት በመፈረጅ በማንአለብኝነት በማሰርና በማሰቃየት ላይ ይገኛል::
  • በቤተክርስቲያንና በቤተክህነት ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአድሏዊነትና ጎሰኝነት አስተዳደር ሲያሰፍን፤ በእስልምናው ኃይማኖት ጉዳይም እንዲሁ ምዕመናኑ ያልፈቀዱትን አስተምህሮ ለመጫን የራሳቸውን መሪዎች እንዳይመርጡ በማድረግና ተወካዮቻቸውን በማሰር እያሰቃየ ይገኛል::
  • ኋላ ቀርና ከፋፋይ የሆነውን የዘር ፖለቲካ መመሪያው በማድረግ ዜጎች በራሳቸው አገር ዉስጥ በሰላማዊ መንገድ ከሚኖሩበት የአማራ ተወላጆች ናችሁ በማለት እንዲፈናቀሉ፣ እንዲባረሩ፣ እንዲሰቃዩም በማድረግ የዘር ማጥራት ወንጀል እንዲከናወን በዋናነት አስተዋፅፆ አድርጓል። ከብዙ ማምታትና ክህደት በኋላም ድርጊቱን በአደባባይ ለማመን ተገዷል::
  • በጋምቤላ የአኝዋክ ተወላጆች ላይ ሰፊ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። በኦሮሞና በሌሎችም ኢትዮጵያዊ ብሔረሰቦች ላይ ከፈተኛ ተደጋጋሚ በደሎችን ፈጽሟል።
  • መንግሥት በሙስና በመበከሉ፣ የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ፣ ሥራ-አጥነት በመብዛቱ፣ የሕዝቡ ብሶት አድማጭ እያጣ ከኑሮ ውድነትና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምረው አብዛኛው ሕዝብ ኑሮውን መምራት ተስኖታል።
ሕዝባችን ይህን ዓይነት አገር አጥፊና ወደፊትም ወደ ከፍተኛ ቀውስ ይዞን እየተጓዘ ያለ፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲዎቸን ሆን ብሎ የሚያራምድ የፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አገዛዝ የተሸከመበት ጫንቃው ከመጠን በላይ ቆስሏል። በዚህ ከሥልጣኑ ባሻገር ምንም ዓይነት ኃላፊነት በማይሰማው ጨቋኝ ቡድን አማካኝነት አገርና ሕዝብ ለአሰቃቂ ጥፋት ሲዳረጉ ዝም ብሎ ማየት አይቻልም። አምባገነኖች ወደዱትም ጠሉትም ሕዝቡ በአደባባይ ወጥቶ ስሜቱን መግለፅ ዴሞክራሲያዊም ተፈጥሯዊም መብቱ ነው። ይህን ደግሞ ሳይውል ሳያድር የሚያከናውነው መሆኑ አያጠራጥርም።
ከዚህም አንፃር በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ በኩል ለግንቦት 17፣ ቀን 2005 ዓ.ም የተጠራውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ወቅታዊና ተገቢ ነው እንላለን:፡ ሃሳብንና ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ የመግለፅ መብት በአገራችንም ሆነ በአለም ዓቀፍ ደረጃ በተደነገጉ ሕጎች ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። በመሆኑም ይህንንም ዓይነት ብሶትን የማሰማትና ተቃውሞን የማቅረብ ጥሪ ሕዝባችንም ሆነ ማንኛውም ሕወኃት/ኢሕአዴግ የሚያካሂደው ግፍና ጥፋት የሚያሳስበው በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈ በሙሉ ሊደግፈው ይገባል። ከመደገፍም አልፎ በተቀነባበረ መልክ ሰላማዊ ሀገር አቀፍና ዓለምአቀፋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ባቀረባቸው ጥሪዎችና አቋሞች በአገራችን ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲስፍን የሚታገሉ ኃይሎች በሙሉ በአንድ ላይ በመቆም አምባገነኑን ሥርዓት እንዲታገሉና በሰላማዊ ሕዝባዊ ትግልም ወደ ትክክለኛና እውነተኛ ሕዝባዊ ሥርዓት እንድንሸጋገር ለመተባበር ያለውንና ያሳየውን ፍላጎት አሁንም በማደስ ማንኛውንም ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ መብቱን ለማስከበርና ብሶቱን ለመግለጥ ከሚሠለፈው ሕዝብ ጎን ይቆማል!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በቆራጥ ልጆቿ ትግል ታፍረውና ተከብረው ለዘላለም ይኖራሉ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

No comments:

Post a Comment