Tuesday, December 9, 2014

የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኢትዮጵያ
ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
ማለዳ ፌስቡክ እንዴት አደረ? ብዬ ስከፍት የተዋናይት ሜሮን ጌትነትን ለወሊድ አሜሪካ ልትሄድ መሆኑን አንብቤ ቴዲ አፍሮ ትዝ አለኝ ። የሜሮን አይገርምም ። አሁን ልጆቻቸው ኢትዮጵያ እንዲወለዱ የሚፈቅዱ ወላጆች ጥቂት ወይም እዚያ የመውለድ እድሉ የሌላቸው ናቸው ። የባለሀብት ፣ የባለስልጣን ፣ የፓይለት ፣ የሆስቴስ ፣ ወዘተ ልጆች አሜሪካ ነው በብዛት የሚወለዱት ። ለብዙዎች ኢትዮጵያ አንደ ቀን አሜሪካ ጠቅለው እስኪሄዱ መሸጋገሪያቸው ናት ። እነዚህ ኢትዮጵያ የልጃቸው መኖሪያ እንድትሆን ያልፈቀዱ ዜጎች "ኢትዮጵያ ሀገሬ እወድሻለሁ " ሊሉ እንዴት ይችላሉ? ሰው እንዴት በእንግድነት ካለበት ቤት ፍቅር ሊወድቅ ይችላል? ምንድነው ሀገር መውደድ? አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እነዚህ ሀገሪቱን ጊዜያዊ መኖሪያ ያደረጉና በቀጣይ ሀገሪቱ የተሻለች መኖሪያነቷ ላይ ጥያቄ ያላቸው ዜጎች የሚበዙቱ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸው ነው ።
በዚህ ስርዓት ቅጠቀጣ የበዛበት ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከሀገር ለመውጣትና እዚያው ለመኖር በቂ ምክንያት አለው ። ድምፃዊው ግን ብልጥ ብቻ ሳይሆን ብልህ ነው ። ከሀገሩ ቢወጣ ከባህር የወጣ አሳ እንደሚሆን ያምናል ። ከነችግሩም ሀገርና ህዝብ እንደሚበልጡ ይረዳል ። ከሀገር ወጥተው ከባህር የወጡትን ያያል ። ከዚህ ሁሉ በላይ ሀገሩን ይወዳል ። ይህች የሚወዳት ሀገሩ ለእሱ ባትመቸው እንኳ ለልጆቹ የመኖሪያ ሀገር መሆኗ ላይ ጥያቄ አላነሳም ። ልጆቹን ለሀገሩ ነው የሰጣቸው ። ስለዚህም ባለቤቱ አምለሰት እርግዝናዋ ገፍቶም እዚያች ለብዙዎች " የተስፋዪቱ ምድር " የሆነች ሀገር ስትቆይ እዚያው እንደምትወልድ ነበር የገመቱት ። አምለሰት ግን ብዙዎች ወደዚያ በሚሄዱበት ወቅት ወደዚህ መጣች ። የቴዲ ልጅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተወለደ ። ይህ ብዙ ማለት ነው ። ትልቅ ውሳኔ ነው ። በሀገር ለመማረርና ሀገርን " ለመጥላት" ፣ ቢያንስ በሀገርና በስርዓቱ (ብዙዎች ዘላቂዋን ሀገርና ነገ የሚወድቀውን ስርዓት ለይተው አያዪም) እምነት ለማጣት ቴዲ ይቀርባል ። ይህ ሁሉ ግን ልጁን አሜሪካዊ ለማድረግ ውሀ የሚቋጥር ምክንያት አልሆነለትም ። ስለዚህ የቴዲን ሀገሬ እሰማታለሁ ። ሀገሬ ሲል እውነትም ሀገሩን እያሰበ ነው ። ቴዲ " ሀገሬ ለእኔ የሙዚቃ ግጥም ማድመቂያዬ አይደለችም ፤ ሀገሬ ናት " ቢለኝ አምነዋለሁ ። ብዙዎች ግን አፋቸው እንጂ ተግባራቸው ይህን አይልም ። የቴዲ አፍሮ ኢትየጵያ በስሟ ግጥም የሚሰራላት ፣ ዜማ የሚንቆረቆርላት ፣ ብር የሚታፈስባት ብቻ አይደለችም ። እንደ ትናንቱ ሁሉ ዜግነቷ የሚወደድ በጭንቅ ውስጥ ያለች የተስፋ ሀገር ናት ። ቴዲ ልጆቹን በጉዲፈቻ ማሳደግ የፈቀደ ክፉ አባት አይደለም ። የሚዘፍንላትና በዘፈኑም ሀብት ያፈራባትን ሀገሩን የንግድ መደብር አላደረጋትም ። መኖሪያውና የልጆቹ ማደጊያ እንድትሆን መርጧታል ። ብዙዊች ግን ፣ የቴዲ ከሳሾችም ጭምር ይህ የሀገርን ሀገሬ የማለትና ባለሀገር የመሆን ሞራላዊ ድፍረት በውስጣቸው የለም ።

Tuesday, December 2, 2014

ዘጠኙ ፓርቲዎች ለቀጣይና ለቀሩ ስራዎቻቸው ያወጡትን እቅድ በተመለከተ መግለጫ ሰጡ።እንዲሁም የህዳር 27 እና 28 የተቃውሞ ሰልፉን እንደሚያካሂዱ አስታወቁ።

ኀዳር ፳፪(ሃያ ሁለትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሺን፣ ፓርቲዎቹ ይህን አስታወቁት ባወጡት መግለጫ ነው።


ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ደብዳቤ ለመቀበል አሻፈረን ሲል የነበረው መስተዳድሩ በፖስታ የተላከለትን ደብዳቤ ከተቀበለ በሁዋላ ከህገመንግስቱና ከአዋጁ ቁጥር 3/1983 ተቃራኒ የሆኑ ምክንያቶችን በመደርደር ለሠላማዊ ሠልፉ ዕውቅና አልሰጠሁም ሲል ህዳር 22 ቀን  ድብዳቤ መጻፉን አስታውቀዋል፡፡
“በመሠረቱ መስተዳድሩ ጊዜና ቦታ እንዲቀየር አስተያየት ከማቅረብ ያለፈ ዕውቅና የመንፈግ መብት የሌለው በመሆኑ ትብብሩ የደብዳቤውን መልዕክት ያልተቀበለ መሆኑንና ሠልፉም በታቀደው ጊዜና ቦታ እንደሚደረግ ወስኖ የመልስ ደብዳቤ ” ማስገባቱንም ገልጸዋል።
የፓርቲዎቹ መግለጫ አያይዞም “ትግላችን ነጻነታችንና ክብራችን የማስመለስ በመሆኑ መንገዱም ፍጹም ሠላማዊ፣ ህጋዊና  ህገ- መንግሥታዊ ስለሆነ የህዳር 27/28  ሠላማዊ ሰልፍ የማይቀርና የማይቀርበት መሆኑን ለመግለጽና ነጻነትና ክብርን ወዳድ ኢትዮጵዊያንና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ለዚህ ታሪካዊ ዕለትና ሠላማዊ ትግል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪያችንን እናቀርባለን።” ብሎአል። 

ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ

ኑ- ለነጻነታችንና ክብራችን ድምጻችንን በጋራ እናሰማ!

ከባርነትና ውርደት ለመላቀቅ ነውና በፍጹም አይቀርም፣ አይቀርም!

የ9ኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ ››በሚል መርህ የመጀመሪያ ዙር ዕቅዱን ለህዳር ወር አዘጋጅቶ ወደ እንቅስቃሴ ከገባ ሦስት ሣምንታትን አሳልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራትና የተጓዝንበትን መንገድ ለጉዳዩ ቀዳሚ ባለቤትና ለባለ ድርሻ አካላት ስናሳውቅ የነበረ በመሆኑ ያጋጠሙንን ችግሮች በመደጋገም ማሰልቸት አንሻም፡፡

ስለሆነም የዛሬው መግለጫችን በቀጣይ ለቀሩን ተግባራት የደረስንበትን ድምዳሜና ያወጣነው ዕቅድ በሚመለከት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ በእስከዛሬው እንቅስቃሴያችን ይዘን የተነሳነው ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› የሚለው መርህ ትክክልና ወቅታዊ፣ ያነሳናቸው ጥያቄዎችም አግባብ መሆናቸውን ያረጋገጥንበትና ገዢው ፓርቲ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለት ፍጻሜዬ ነው በሚል ከገባበት ከፍተኛ የፍርኃት ስሜትና ሥጋት ለተቃውሞ ጎራው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በሩን ለመዝጋት የተዘጋጀ መሆኑን አገር ለ23 ዓመታት በላይ ካስተዳደረ መንግስታዊ ሥርዓት የማይጠበቅ መረን የለቀቀ የውንብድና ተግባራት ያረጋገጥንበት ነው፡፡ በመሆኑም ጥያቄዎቻችንን በህገ መንግስቱና በአገሪቱ ህጎች መሠረት ለመመለስ ቀርቶ ለመስማትና ለማንበብ ፍቃደኝነቱና የኃላፊነት ስሜቱ እየተሟጠጠ በመሆኑ የአፈናና ማስፈራራት መንገድን ብቸኛ አማራጭ አድርጎታል፡፡ ይህ በመሆኑም የራሱን መንግሥታዊ መዋቅር አሰራር ሥርዓት እንኳ በአደባባይ ለመቀበል እምቢተኛ መሆኑን በአደባባይ አረጋግጧል፡፡ ባለሥልጣናቱ በግንባር ያቀረብነውን ደብዳቤ ካለመቀበል አልፈው በመንግሥታዊው ፖስታ ቤት የተላከ ደብዳቤ ያለመቀበላቸው የሚያመለክተው ይህንና የደረስንበትን የመልካም አስተዳደር አዘቅት ነው፡፡

በተቃራኒው አበረታችና መልካም ዜናም አለ፡፡ ይህም ይህን የአፈናና ማስፈራትት አካሄድ አንቀበልም ያሉ ለነጻነታቸውና ክብራቸው፣የራሳቸው ብቻ ሣይሆን የመንግሥት መዋቅሮችና ባለሥልጣናትም ነጻነት መረጋገጥ አለበት ብለው የቱንም መስዋዕትነት ለመክፈል በቁርጠኝነት የተዘጋጁ በትብብሩ የታቀፉ ፓርቲዎች፣ አመራርና አባላት መኖራቸውና በትግሉ ለመቀጠል መወሰናቸው ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ትብብሩ ለመጀመሪያ ዙር ዕቅዱ ማጠቃለያ የህዳር 27/28 የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ አመራሩ በግንባር ቢያቀርቡም አሻፈረኝ አንቀበልም ያሉት አሰራርና ባለሥልጣናት ከፖስታ ቤት እንዲቀበሉ ተደርጓል፡፡ለዚሁ ደብዳቤ መስተዳድሩ ከህገመንግስቱና ከአዋጁ (ቁጥር 3/1983) ተቃራኒ የሆኑ ምክንያቶችን በመደርደር ለሠላማዊ ሠልፉ ዕውቅና አልሰጠሁም ሲል በዛሬው ቀን (22/03/07) መልስ አድርሶናል፡፡ በመሠረቱ መስተዳድሩ ጊዜና ቦታ እንዲቀየር አስተያየት ከማቅረብ ያለፈ ዕውቅና የመንፈግ መብት የሌለው በመሆኑ ትብብሩ የደብዳቤውን መልዕክት ያልተቀበለ መሆኑንና ሠልፉም በታቀደው ጊዜና ቦታ እንደሚደረግ ወስኖ የመልስ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡ በመሆኑም ለተግባራዊነቱ ዝግጅቱን በሙሉ አቅም ጀምሯል፤ ለዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከአገር ውስጥና ከውጪ አጋርነታቸውን ገልጸዋል፤ አበረታተውናል፡፡ ይህም የያዝነው የትብብር የጋራ ዓላማችን ተቀባይነት፤ የኅብረትና አንድነትን ዋጋ አመላካች፣ ለማይቀረው ሠላማዊ ትግላችን ሥንቅ ነውና በታላቅ አክብሮት ተቀብለነዋል፡፡

ስለሆነም ይህ መግለጫ ትግላችን ነጻነታችንና ክብራችን የማስመለስ መንገዱም ፍጹም ሠላማዊ፣ ህጋዊና ህገ- መንግሥታዊ ስለሆነ የህዳር 27/28 ሠላማዊ ሰልፍ የማይቀርና የማይቀርበት መሆኑን ለመግለጽና ነጻነትና ክብርን ወዳድ ኢትዮጵዊያንና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ለዚህ ታሪካዊ ዕለትና ሠላማዊ ትግል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ነጻነታችንና ክብራችን ለማስመለስ ዋጋ ለመክፈል እንዘጋጅ፣ ያለመስዋዕትነት ድል የለምና!