Monday, November 17, 2014

ለሃገር መከላከያና ለፖሊስ ሰራዊቱ ፤ እንዲሁም ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አባላት በሙሉ የቀረበ ሃገራዊ ማሳሰቢያ፤
በጥቂት ፈላጭ ቆራጮች የሚመራው የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ሃገርን የማጥፋትና ህዝብን የመነጣጠል እኩይ ዘመቻ፤ ኤርትራን በማስገንጠል ተጀምሮ፤ ዛሬ ውድ ዜጎቻችን ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው በግፍ ተገፍተውና በየሜዳው ተወርውረው በረሃብ እየማቀቁ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ መሬትና ሃብት ፍፁም ግዴለሽ በሆነ መልኩ፤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ብቻ በዉለታ ለባዕዳን ሃገራት አየተሰጠና ይህ ነው የማይባል ፋይዳ በሌለው ቤሳበስቲን አየተቸበቸበ ይገኛል። ለዘመናት በደም ተጠብቆና ተከብሮ የኖረው የማንነታችን መገለጫ አርማችን፤ ሰንደቅ አላማችን፤ ክብር ተነፍጎ በየስርቻው ጨርቅ ነው ተብሎ አየተጣለ ይገኛል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘበው እነኝህ ጥቂት አምባገነኖች ላለፉት 23 አመታት በሃገርና በህዝብ ላይ በማናለብኝነት ያደረሱትን ግፍና መከራ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስታስፈጽሙና በቸልተኝነት እንደ ባዳ ስትመለከቱት እንደነበራችሁ ይታወቃል። ይሁንና ይህ ሁሉ በደል ሲደርስ አንጀታችሁ እያረረ ልባችሁ በሃዘን እየተሰበረ ምንም ማድረግ ሳትችሉ የቆያችሁበት ምክንያት ሥርዓቱ ያደርስባችሁ በነበረው ከፍተኛ ተፅዕኖና አፈና መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ይረዳል። ነገር ግን ይህን ጠንካራ የህዝብ እምነት የምታረጋግጡት እናንተና እናንተ ብቻ መሆናችሁ የሁሉም ህብረተሰብ እምነት ነው።
ዛሬ ሁላችሁም በጥልቀት መርምራችሁ በማስተዋል መፍትሄዎችን ልታበጁባቸው ግድ የሚሉ ዘርፈብዙ ችግሮች ከፊት ለፊታችሁ ተደቅነዋል። እስከመቼ የጥቂቶች የበላይነት በሃገራችን ነግሶ ይኖራል!? እስከመቼስ በዚህች ታላቅ ሃገርና በክቡር ህዝባችን ላይ የሚደርሰው በደል እንዲቀጥል እንፈቅዳለን!? እስከመቼስ ጥቂቶች በእናንተ ትከሻና ጉልበት ተጠቅመው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብን ሲጨቁኑ ይኖራሉ!? እስከመቼስ ጥቂት የህዝብ ጠላቶችን ስልጣንና ጥቅም ለማስከበር አገልጋይ ሆናችሁ በዝምታ መኖር ይቻላችሁ ይሆን!? እስከመቼስ በጥቂቶች ቀጭን ትዛዝ የምትወዱትን ንፁህ ወገናችሁን ስታሳድዱና ስትገሉ ትኖራላችሁ!? እስከመቼስ በጥቂት ግለሰቦች ጭፍን ትዕዛዝና በናንተ ፈፃሚነት ብዙዎች ሲሰቃዩና ሲጎዱ ይኖራሉ!? የዚህ ሁሉ ችግር ምንጮች ጥቂት አምባገነን ገዚዎቻችን ቢሆኑም፤ መፍትሄው ግን በጃችሁና በጃችሁ ይገኛል።
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች! ዛሬ ይህ ለሃገራችሁ የሚጠበቅባችሁን ሃላፊነት በአግባቡ እንዳትወጡ በተለያዩ አፈናዎች ጠፍንጎ መፈናፈኛ በማሳጣት፤ አዋርዶ የምትወዱትን ህዝብና ሃገር ጎድታችሁ የጥቂት አምባገነኖችን ስልጣንና ጥቅም ለማስጠበቅ አገልጋይና ሎሌ ሆናችሁ እንድትቀሩ እያስገደዳችሁ የሚገኘው ጨቋኝ አገዛዝ፤ በህዝብ ትግል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገድበት ወቅት መድረሱ እሙን ሆኗል። ይህ ታላቅ ህዝባዊ ድል የተገኘው እንደው ዝም ብሎ በመመኘት ሳይሆን፤ በመላው ኢትዮጵያውያን በዋነኝነት ደግሞ በወጣት ወገኖቻችሁና ልጆቻችሁ የተገነባው ህዝባዊ ንቅናቄ ባካሄደው በሳል ስትራቴጂ፣ ትግልና፣ መስዕዋትነት መሆኑን እንደምትረዱ እናምናለን። ይሁንና ይህ የተቀደሰ የትግል ጅማሮ ፍፃሜው እናንተን ጨምሮ፤ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃነት ሊያረጋግጥ የሚችለውና በውጥኑ መሰረት ለሁሉም እኩል የሆነችና ከቂም በቀል የፀዳች ሠላማዊት ሃገርን መገንባት የምንችለው፤ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቆራጥ ትግልና ርብርብ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል። ይህ ህዝባዊ ትግል፤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ እናንተም የህዝባችሁን ህልውናና የሃገራችሁን ዘለቄታዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከህዝብ ጎን በቁርጠኝነት ተሰልፋችሁ በፅናት በመታገል፤ ነፃነታችሁን የምታረጋግጡበት ወሳኝና መልካም አጋጣሚ ነው። በመሆኑም በቀጣይ በሚደረገው ህዝባዊ የትግል ሂደት ለብዙሃኑ ህዝብ ከለላ በመሆንና ወገንተኝነታችሁን በተግባር በማሳየት፤ ብሎም ህዝብ የጣለባችሁን ከፍተኛ ሃገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት፤ ታሪካችሁን አድሳችሁ በክብር መዝገብ ላይ ታሰፍሩ ዘንድ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚጠብቅ ተገንዝባችሁ፤ የሚጠበቅባችሁን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንድትሆኑ ስንል ከታላቅ ሃገራዊ አደራ ጋር እናሳስባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment