Monday, April 14, 2014

በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብ በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ


 በ11-4-2014 በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብና ኖርዌ በስደተኛው ላይ ያላትን ፖሊሲ በመቃወም    የተቃውሞ ሰልፍ አረጉ።  23 ዓመት እራሱ መራጭ እራሱ ተመራጭ ሆኖ በጠመንጃ አፈሙዝ ህዝቡን እያንቀጠቀጠ የኖረው ወያኔ አንድ ቀን ሕዝብ በቃኝ ብሎ አንቅሮ እንደሚተፋውና ንብ ሆኖ ለነፃነቱ እንደሚነሳ ማወቅ ነበረበት።
ግን አልሆነም ዜጎች እንደዜጋ በሐገራቸው መኖር ቀርቶ በስደትም ሰላማቸውን ማግኘት አልቻሉም።
እስርና እንግልት፣ረሐብና ሰቆቃ፣ስደት የእያንዳንዱ እጣ ፋንታ ሆነ፤በወያኔ ዘመን ሰው ብቻ አይደለም መሬትም መሰደድ ጀምሮ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል የኢትዮዽያን ለም መሬት ለሱዳን በመሸጥ ላይ ይገኛል
ኢትዮዽያንና ኢትዽያዊነትን ያሉ ሁሉ አሸባሪ እየተባሉ በየእስርቤቱ ታጉረው እጣ ፈንታቸው እስርና እንግልት ሆነ ሐገራቸውን ጥለው በባሕርና በየብስ አቆራርጠው የሞተው ሞቶ የተረፈው በአለም ዙሪያ ተበትኖ ጥገኝነት  በመጠየቅ ይኖራል::
በዚሕም የተሳካላቸው ጥቂቶች ሲሆኑ ባብዛኛው ወያኔ ለውጩ አለማት በሚያሳየው ሁለተኛው ፊቱ ምክንያትና ምእራባውያን ከሐገሪቱ ከሚያገኙት ጥቅም የተነሳ ሐገርህ ዲምክራሲ ነው እየተባለ ፍትሀዊ ያልሆነ መልስ እየተሰጠው በመጉላላት ላይ ይገኛል።
ያም ሆኖ የሐገሩ ጉዳይ በደም ስሩ ሰርጎ የገባው ኢትዮዽያዊ ሁሉ ጠዋት ማታ ኢትዮዽያዬ እያለ ይጮሀል። ይህ የህዝብ ቁጣ ያስፈራው ወያኔ ያለ የሌለ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ እየመዘበረ ዜጎችን ይሰልላል ያሰልላል፣አልፎ ተርፎም ዜጎችን ከመሰሎቹ ጎረቤት ሐገሮች ድረስ በመሄድ ጎትተው እስርቤት ያስገባሉ።
ይህንን ለመቃወምና ለማውገዝ ነበር የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ኢትዮዽያውይኑ ዛሬም ስለ ሐገራቸው ሊጮሁ የወጡት፤ ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን እንዲህ በማለት ነበር ድምፃቸውን ያሰሙት እኛ ስደተኞች እንጅ ወንጀለኛ አይደለንም፣ኖርዌ ለማፊያው ወያኔ የምታደርጊውን እርዳታ አቁመሽ ከኢትዮዽያ ሕዝብ ጋር ቁሚ፣ወያኔ የሚያደርገውን ተግባር እናወግዛለን፣ሼም ኦን ዩ ሳውዝ ሱዳን ኦኬሎን አሳልፈሽ የሰጠሽ፣ወያኔ አሸባሪ ነው፣ለውጥ እንፈልጋለን፣ኖርዌ የዩኤንን ህግ ታክብር የሚሉትን የመሳሰሉ ሲሆን
በሰልፉ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮዽያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ተወካይ አቶ ዳንኤል የወያኔን ጀሌዎች የማጋለጡ ስራ በሚገባ እየተሰራበት መሆኑን ሲገልጡ ሰልፈኛው በጭብጨባ የተቀበላቸው ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም ተወካይ ኖርዌ ነፃ እንድታወጣን ሳይሆን ለወያኔ የምትሰጠውን እርዳታ አቁማ ድጋፍ እንድትሰጠን ነው፤ በተጨማሪም ኖርዌ አቶ ኦኬሎን ታስለቅቅ በማለት  ተጠይቃለች። በሰልፉ ላይ የኖርዌ ሊብራል ፓርቲ ተወካይ ከሰልፈኛው ደብዳቤ ተቀብለው መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኖዋስ ፣አንቲረሲስት ተወካዮችም እንዲሁ ይዘውት የመጡትን መልክት ለሰልፈኛው አስተላልፈዋል።
ከዚያ በቀጥታ ወደሶፊን በርግ ሎካል አዳራሽ ሰልፈኛው አምርቶ ምሳ  ከተበላ በሁዋላ ኮሚቴው ካባላቱ ጋር ሰፊ ዉይይት ያደረገ ሲሆን የ፫ወር የስራ ሪፖርትም አቅርቦአል።
የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ

የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ በኖርዌይ ኦስሎ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ


በዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ  የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አዘጋጅነት አፕሪል ቅዳሜ 12/2014  በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ  የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሄደ:: በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከኦስሎ እና ከተለያየ ከተማ  በመምጣት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን  የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል::
ሕዝባዊ ስብሠባው በኖሬጅያውያን የሰአተ አቆጣጠር ከቀኑ 15:00 እስከ ምሽቱ 21:00 ሰዓት የተካሄደ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ  አቶ አቢ አማረ በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አረመናዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ አስር ቤቶች በፖለቲካ ኣስተሳስባችው ምክንያት ያለወንጀላች የሚስቃዩ ውድ ኢትዮጵያዊን ወገኖቻችን በማስብ  በዚሁ ዘረኛ ቡድን አስቃቂ የኣካል ጉዳት ለተፈጸባቸው ኢትዮጵያዊን  የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማስደረግ ስብሰባውን አስጀምረውታል::

በመቀጠለም አቶ ዮሀንስ አለሙ የዴምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ስለ ዲምክራሲያዌ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አመሰራረት እና ስለ ድጋፍ ድርጅቱ አላማ በማብራራት የድጋፍ ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት በሀገር ቤት በሰላማዊ ትግል የወያኔን መንግስት ለመጣል እየታገሉ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶችን እየረዳ እንደሚገኝ እና ከሀገር ውጭ ደግሞ የወያኔን መንግስት  በሁለገብ ትግል  ለማስወገድ እየሰራ ያለውን የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅትን በግንባር ቀደምነት እየረዳ እንዳለ በመግለጽ  የወያኔን ዘረኛ ስርአት ለመጣል ሁሉም ሰው አስተዋጿ ማድረግ እንደሚጠበቅበት እና ማንኛውም  ኢትዮጵያዌ ዜጋ በሀገራችን የጋራ ጉዳይ ስለሆነው  የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሀሳብ በመለዋወጥ ፣በመካከላችን ያሉትን ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ኋላ በመጣል ፣ በመቻቻል፣ ሀገር እያፈረሰ እና ሕዝብ እያዋረደ ያለውን የዘረኛውን የወያኔን መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁለገብ ትግል ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበት አጽኖት ሰተው ንግግር አድርገዋል::
በመቀጠለም ዲምክራሲያዊ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል የሆኑት አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ ሰፊውን ጊዜ በመውሰድ ከንጉሱ ስርአት ጀምሮ በደርግ መንግስት ዘመንም በሀገራችን የተደረጉ የፖለቲካ ንቅናቄዎችንና ለውጦችን አንድ በአንድ በመዘርዘር አሁን ካለው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ጋር በማነጻጸር ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ላይ ሀገሪቱን እየመራው ነው የሚለው የወያኔ መንግስት ከዚህ ቀድሞ ኢትዮጵያን ከመሩት ከሁለቱ መንግስታቶች ማለትም ከንጉሱም ከደርግም መንግስት ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ እንደማይገናኝ የወያኔ መንግስት ዘረኛና የዘረኝነት ፖለቲካ እያራመደ ያለ አረመናዊ መንግስት እንደሆነ አብራርተዋል::
የግንቦት 7  የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ አክለውም ከወያኔ በፊት የነበሩ ሁለቱ መንግስታቶች ለውድቀት የዳረጓቸውን ምክንያቶች በመጥቀስ የወያኔን አንባ ገነናዊ መንግስት ለአፋጣኝ ውድቀት ሊዳርጉት ይችላሉ የሚሉትን ግልጽ ምክንያቶች በመዘርዘር አስቀምጠዋል:: አቶ ቡዙነህ በሁለት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማንሳት እና በማብራራ ከሕዝብ ውይይት እንዲያደርጉበት ለመወያያ ያቀረቡ ሲሆን እነዚህም
1, በሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በወያኔ መካከል ያለው ግጭት
2, የህዳሴ ግድብን  በማስመልከት ያለው ተቃውሞ
ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሲናገሩ የሙስሊሙ ትግል በሁለት አመታት ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ትግል በጣም የተሳካና ወያኔ በቀላሉ ሊያዳፍነው ያልቻለው ሰላማዊ መብትን የመጠየቅ ትግል እንደሚያደንቁ በመናገር ነገር ይህ በሙስሊም ማህበረሰብ በኩል እየተደረገ ያለው ትግል እስከ አሁን ድረስ ከመንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ሊያገኝ እንዳልቻለ እና ወደፊትም ከወያኔ መንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል:: ለዚህም ማስረጃው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከጠየቋቸው አራት የመብት ጥያቄዎች አንዱም ካለመመለሱ በተጨማሪ እስካሁን መሪዎቻቸውም በሃሰት ውንጀላ በእስር እየማቀቁ ያለፍርድ እየተንገላቱ መሆናቸው ነው፥፥
ነገር ገን አሁን እየሆነው ባለው ሁኔታ በእንደዚህ አይነት መንገድ እስከመቼ ድረስ የሙስሌሙ ትግል ይቀጥላል በማለት የተናገሩ ሲሆን አሁን እየሄደ ባለው አካሄድ የሙስሊሙ ተቃውሞ የትግል አቅጣጫውን እስካልቀየረ ድረስ ረጅም ርቀትን ትግሉ ሊቀጥል ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ነግር ግን የሙስሊሙ ጥያቄ ከእምነት መብት ጥያቄ ባሻገር ወደ የዜግነትን መብት ወደ ማስከበር መለወጥና መሸጋገር  እናደለበት በመናገር የሙስሊሙ ማእበረሰብ ጥያቄ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው  ትግሉ በዚህ መልኩ ሲቀጥል እንደሆነ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰተዋል:

በሁለተኛም የህዳሴ ግድብ በሚመለከት  ያቀረቡት ሀሳብ ወያኔ የራሱን የፖለቲካ ኪሳራና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ በዕድገት ስም ለመሸፈን ያመጣዉ እንጂ ታቅዶበትና ለህዝቡ በማሰብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉ ግፍ እንደ ማስረጃነት በማቅረብ ያብራሩ ሲሆን እንደ ምሳሌም ወያኔ ሃገራዊ የሆነ አላማ ይዞ ካለመነሳቱ አንፃር የሃገርን ድንበር አሳልፎ እስከመስጠት እየሄደ ያለበትን ሁኔታ ጠቅሰው ይህ አሰራር ደግሞ የዲክታተሮች ባህሪ እንደሆነ አብራርተዋል፥፥

የወያኔ መንግስት በህዳሴ ግድብ ሰበብ ምክንያት በማድረግ በመላው አለም ኢትዮጵያኖች በሚኖሩበት ሀገሮች በመዞር የዲያስፖራውን ቀልብ ለመውሰድ የሚያደርገው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ሩጫ በዲያስፖራ ተቃዋሚዎች አማካኝነት በፍጹም እንዳልተሳካለት ይህንንም የወያኔ በአባይ ቦንድ ሽያጭ ስም ገንዘብ ዘረፋ በመቃወም ወያኔን አሳፍረው ከመለሱት መካከል በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እንደሆኑ በማስታወስ  የዚህ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰበብ የወያኔን መንግስት ወደ መጥፎ ውድቀት ላይ ሊጥለው እንደሚችል በማመን የወያኔ መንግስት በአሁን ሰአት ከግብጽ መንግስት ጋር እየገባ ያለው ሰጣ ገባ ለኢትዮጵያ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃለዋል፥፥

በመቀጠልም አቶ ብዙነህ ባነሷቸው ነጥቦችና እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰፋ ያለ ውይይትም ተደርጓል፥፥ ከውይይቱም በማስቀጠል የዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንሄል አበበ የዲምክራሲያዌ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የአቋም መግለጫ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ድርጅታቸው ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ፈጽመው እንደሚያወግዙ እና ዴምክራሲያዌ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሁል ጊዜ ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ ጎን እንደሚቆም ቃል በመግባት የአቶ ቡዙነህ ፅጌን በኖርዌይ በመገኛት ለህዝቡ ለሰጡት ገለጻ አመስግነዋል፥፥
በዝግጅቱ መጀመሪያና ማጠቃለያ ላይ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል መዝሙር በመዘምራን የተዘመረ ሲሆን በየጣልቃው የተለያዩ የባህል ዘፈኖች በተወዛዋዦች ታጅቦ የቀረበ ሲሆን ጣእም ያለው ባህላዊ ምግብም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የሴቶች ክፍል ተስተናግዷል፥፥ ስብሰባውን ተጀምሮ እስኪያልቅ አቶ ፍቅሬ አሰፋ መርተውታል::

በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላችሁን ላበረከታችሁና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች ረዥም ርቀት በመጓዝ የዝግጅቱ ታዳሚ ለነበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን እና እንዲሁም የድርጅቱ አባላቶች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፥፥


ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

Sunday, April 13, 2014

በኖርዌይ የሚገኙ የወያኔ ሰላዮችን በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኦስሎ ከተማ ተካሄደ

በኖርዌይ የሚገኙ የወያኔ ሰላዮችን በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኦስሎ ከተማ ተካሄደ
ማርች 11, 2014 በኖርዌ የሚገኘው የኢትዮጵያን የስደተኞች ማህበር ያዘጋጀው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች በመጡ ታዳሚዎች እና በኦስሎ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ባንዲራ እንዲሁም በተለያዮ መፈክፎች ታጅቦ በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ።

የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ዋና አላማ በኖርዌ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው በሚኖሩበት ሐገር እንደሚሰለሉ እና የወያኔ ሰላዮች በኖርዌይ ምድር መኖራቸውን የኖርዌ የደህንነት ፓሊስ ለሀገሪቱ ትልቅ ጋዜጣ መረጃ መስጠታቸውን እና በተመሳሳይ የሂውማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ የኖርዌ መንግስት ለወያኔ ሰላዬዮች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም እና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ እና ኖርዌ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያላትን የአሳይለም ፖሊሲ እንድታስተካክል የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር።
ፕሮግራሙ ከቀኑ 12፡00 የተጀመረ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ምክትል ሊቀመንበር ሰፋ ያለ የወያኔ ሰላዮችን የተመለከተ ንግግር ያሰሙ ሲሆን የዚሁ ድርጅት የሴቶች ክፍል ተወካይ ወ/ሪት ሔለን ንጉሴ አጠቃላይ በኖርዌ ያሉ ሰላዮችን እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ሴቶች በሁለገብ ትግል ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና እንዲሁም ወደፊት ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና ጨምረው በማስረዳት ለትግሉ አጋር መሆናቸውን ገልፀዋል። በመቀጠል የስደተኛ ማህበሩ ፀሐፊ ወ/ሪት የሺሃረግ በቀለ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያቀረበች በመሆኑ የሐገሪቱ ዜጎች መልክቱን በደንብ እንዲሰሙ ያደረገች ሲሆን የኖርዌጅያን ተወላጅ የሆኑትና በስደረኞች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች በተመሳሳይ ስለ ኢትዮጵያ አምባ ገነን መንግስት ከስደተኛው በላይ የሚያውቁትን መረጃ በዝርዝር በየተራ በንግግር አሰምተዋል። ይህንን የሰላማዊ ሰልፍ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የመሩልን የስደተኛ ማህበሩ የኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ ዮናስ እና አቶ ጌታቸው ናቸው።
በመጨረሻም ከሰላማዊ ሰልፉ በኋላ በወ/ሮ ሰዋሰው እና በባለቤታቸው የተዘጋጀ የምሳ ግብዣ የተከናወነ ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም የውይይት ጊዜ አዘጋጅቶ የነበረ በመሆኑ የስደተኛ ማህበሩን የሶስት ወር ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በቀጥታ ወደ ውይይት በመግባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዌ ስለሚገኙ የወያኔ ሰላዮች በሰፊው ምክክር አድርገው ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዴት እነኚህን ሰላዮች በምን መልኩ ማጋለጥ እንዳለባቸው ተወያይተው በመቀጠል አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት አድርገው ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ ከምሽቱ 19፡00 ተጠናቋል።

Sunday, April 6, 2014

ሃያ ሶስት  አመታት ለኢትዮጵያ እንደምን ያሉ አመታት ነበሩ?

1.ሃያ ሶስት የወያኔ አመታት ለመጀመሪያ ግዜ በሃገራችን ታሪክ ከአንድ ዘር ብቻ የተሰባሰቡ ጥቂት ግለሰቦች የሃገሪቱን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስልጣን፤ የሃገሪቱን ሃብት፣ መሬቱንና ማዕድኑ፤ የሃገር ውስጥና የወጭ ሃገር ንግዱን፤ የኮንስትራክሽን፣ የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የትራንስፖርት፣ የማምረቻና ማከፋፈያ ስራውን የተቆጣጠሩበት፤ እፍረትና ይሉኝት የለሸ ነውረኛና አደገኛ ስራ የተሰራባቸው አመታት ናቸው።
2.ያለፉት 23 አመታት ሃገሪቱ በጥቂት ለዘረፋ ስልጣን በያዙ ዘረኞችና አፋኞች እጅ በመወደቋ ታላቅ የተፈጥሮና የሰው ሃብቷንና እንዲሁም ባለፈው 23 አመታት የተገኘው አንጻራዊ ስላም ተጠቅም ድህነትን ረሃብን ስደትን ሀገራዊ ውርደትን ማስቆም የምትችልበትን እጅግ ታላቅ እድል ያባከነችባቸው አመታት ናቸው።
3.ያለፉት 23 አመታት፣ በየትኛዎቹም ኢትዮጵያ መንግስታዊ ስርአቶች ከቶ ተደርገው የማይታወቁ፤ በሃገራችንና በህዝቧ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ሃገራዊ ክህደቶች የተፈጸሙባቸው አመታት ናቸው። ኢትዮጵያችን ከዚህች ሃገር ውስጥ በወጡ ልጆቿ ሳይሆን ለሃገሪቱና ለህዝቧ ከፍተኛ ጥላቻ ባላቸው፤ ሃገሪቱንና ህዝቧን መበቀል የግድ የሆነባቸው፤ ቂም አዝለው ስልጣን በያዙ የውጭ ወራሪዎች እጅ የወደቀች እስክትመስል ሃገራዊና ህዝባዊ ክብሯ አጥታ የተዋረደችባቸው አመታት ናቸው።
4.ያለፉት 23 አመታት በየትኛውም ዘመን ስልጣን ላይ የወጡ ገዥዎች አስበውትና አድርገውት በማያውቁት ደረጃ የሃገር ሃብትና ቅርስ ስልጣን ላይ ባሉ ጥቂት የትግራይ ገዥ ጉጅሌ አባላት እየተዘረፈ በባእድ ሃገራት የተከማቸበት አመታት ናቸው። እኝህ አመታት የዘረኛው ገዥ ጉጅሌ አባላት ለዘረፋ እንዲያመቻቸው ያስጠጓቸው የውጭ ሃገራት ዜጎች በሃገራችን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የህዝቡን ለም መሬት፣ ወርቅ ሌላም ማእድን እንዳሻቸው እየዘረፉና የሃገሪቱን ህዝብ ከባርነት ስርአት ባለተናነሰ የጌታና የሎሌ ግንኙነት እንዳሻቸው እያዋረዱ እንዲያሰሩ ስድ የተለቀቁባቸው አመታት ናቸው።
5.ያለፉት 23 አመታት ዳኝነትና ፍትህ የሚባል ነገር ጭራሽኑ ካገር የጠፋበት፤ ዜጎችና ህዝቦች ተቆጪ በሌላቸው በዘርና በጥቅም በተሳሰሩ የገዢው ጉጅሌ የጦር አዛዦች፣ የደህንነት አባላትና ካድሬዎች እንዳሻቸው የሚረሸኑበት፤ ህዝብ ለሰቆቃና ለእስራት የተዳረገበት፤ ሰው በገዛ ቤቱ ውስጥ ሳይቀር የሚሰማውን መናገር እንዳይችል የስጋትና የፍርሃት ቀንበር ውስጥ የወደቀችባቸው፤ እንዲሁም በዘር ማጥፋትና በሰው ልጆች ላይ እንደተፈጸሙ ተደርገው የሚታዩና በአለምአቀፋዊ ወንጀለኛነት የሚያስጠይቁ ታላላቅ ወንጀሎች በመላው ሃገሪቱ ህዝብ ላይ የተፈጸሙባቸው አመታት ናቸው።
በጥቅሉ ያለፉት 23 የወያኔ የግዛት አመታት የኢትዮጵያን ውርደት፤ የህዝቧን የድህነት፣ የባርነትና የሰቆቃ ህይወት በማየት በሚደሰቱ ጸረ ሃገርና ህዝብ ሃይሎች እጅ ወድቃ አበሳዋን ያየችባቸው አመታት ናቸው። ግንቦት 20 የተባለውን የዛሬውን የወያኔዎች በአል የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስበው፣ በሃዘን በቁጭትና በንዴት ነው። የወያኔ እድሜ እንዲረዝም ሳይሆን እንዲያጥር በመመኘት፣ በመጸለይ፣ በመደራጀትና በመታገል ነው። የግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ስሜትም ከህዝብ ስሜት የተለያ አይደለም። ለዚህም ነው በወያኔ የፈንጠዝያ እለት ውደቀታቸው የማይቀር መሆኑን የምናረዳቸው።

ውድመት ለዘረኛውና ለዘራፊው ጸረ-ሃገርና ጸረ -ህዝብ ጉጅሌ

እርገት ለኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት የእኩልነት የፍትህና የአንድነት ፍላጎት
from  GINBOT 7

Saturday, April 5, 2014

አንድነቶች በደሴ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያክል ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ዋሉ!
ነገ መጋቢት ሃያ ስምንት በደሴ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለ መሬት ነጻነት” በሚል አንድነቶች ለጠሩት ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በፓርቲው አመራሮች የተመራ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ውለዋል። ቅስቀሳውን እንደተለመደው በመንግስት “ፖሊስ” እና “ድሀንነት” ናችሁ አይዟችሁ የተባሉ ግለሰቦች ሊያደናቅፉት ሞከረው ነበር። ነገር ግን የደሴ ህዝብ እምቢኝ… አላቸው! እናም ቅስቀሳው ዋናው ሰልፍ እስኪመስል ድረስ ደምቆ ውሏል።
የአዲሳባውን ሰለፍ ለሌላ ቀን አስተላልፉልን የተባሉት አንድነቶች “ለበጎ ነው” በለው ደሴ በመከተም ነገ ጮክ ብለው የህዝቡን ጥያቄዎች ከህዝቡ ጋር ሆነው ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል… እኛም፤ “በሰላም ወጥታችሁ በሰላም እነደትገቡ ይመኝላችኋል መላ ህብረተሰቡ…” እንላቸዋለን!
ከአንድነት ለጆች ፌስ ቡክ ገጽ ያገኝሁትን የቅስቀሳውን መልክ የሚያሳዩ ፎቶዎች በደረ ገጻችን ውስጥ አስቀምጪያለሁ
10014636_835747803108349_5128751414974920860_n
10167938_615612508523687_6590304698073775887_n10169280_835744596442003_2820830627681599915_n10172798_835664629783333_3002815242977839681_n10175026_835747739775022_5157766003846390736_n
ወያኔ እንደ ግንቦት ሰባት የኮነነዉና የህዝብና የአገር ጠላት አድርጎ የሳለዉ ድርጅት የለም፤ የወያኔ የዜና ማሰራጫዎችም ይህንን የአገዛዙን አቋም በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰምተዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ማን ለመብቱና ለነጻነቱ እንደቆመና ማን መብቱና ነጻነቱ ላይ እንደቆመበት ለይቶ የሚያዉቅ ህዝብ ነዉ። ስለዚህም ግንቦት ሰባት ወያኔዎች አላፊዉንና አግዳሚዉን “ግንቦት ሰባት” ነህ እያሉ ከሚያሰቃዩ፤ ህዝብንና ግንቦት ሰባትን ያስተሳሰረዉ ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ነዉና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ቢመልሱ ለእነሱም፤ ለእኛም ለአገርም ይበጃል የሚል የጸና እምነት አለዉ። ወያኔ በኢህአዴግ ስም ያሰጠጋቸዉን ምሰለኔዎች ጨምሮ ከራሱ ዉጭ ሌላ ማንንም አያምንም፤ ስለዚህም ነዉ የአገሪቱን የመከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ተቋሞች በራሱ ሰዎች ቁጥጥር ስር ያደረገዉ። ዛሬ በግልጽ እንደምንመለከተዉ ወያኔ በጉልበት ለያዘዉ ስልጣን ያሰገኛል ብሎ በሚጠረጥረዉ ቦታ ሁሉ የራሱን ልዩ ሚሊሺያ እየለላከ የኢትዮጵያን ህዝብ መኖሪያ ቤቱ ድረስ አየሄደ እያጠቃ ነዉ። ግንቦት ሰባት ወያኔና የፈጠረዉ ዘረኛ ስርዐቱ የቆሙት በፍጹም ማንሰራራት የማይችሉበትት የመጨረሻ መቀበሪያ ጉድጓዳቸዉ ጫፍ ላይ ነዉ የሚል ጽኑ እምነት አለዉ። ሆኖም ጉድጓድ ጫፍ ላይ የቆመ ጠላት በራሱ ተወርዉሮ ጉድጓዱ ዉስጥ አይገባምና ይህንን የተዳከመ ጠላት እተፈራገጠ ጉዳት ከማብዛቱ በፊት ለመደምሰስ ክንዳችንን አጠናክረን በህብረት እንደ አንድ ሰዉ እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

“ውሃ፣ መብራት፣ ኔትዎርክ የለም ፤ ኑሮ ከበደን” ሰሚ ጆሮ ያጣ የሕዝብ እሮሮ

“ውሃ የለም፤ መብራት፤ ኔትዎርክ የለም፤ መብት የለም፤ ፍትህ የለም፤ ኑሮ ከበደን” እያሉ ስለኑሮዓቸው የተሰማቸውን በሀቅ የተናገሩ ልጃገረዶች በጋጠወጥ የህወሓት ካድሬዎችና ታጣቂዎች እጅ መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ ለጋ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ በዝምታ ያልፋል ተብሎ አይታመንም።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮን ጨምሮ በወያኔና የጥቅም ተጋሪዎቹ ሥር የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን በየዕለቱ ያለማቋረጥ ከሚዘገቡት የልማትና የዕድገት ዘገባዎች ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዘው በአገራችን ውስጥ እየተሠሩ ስላሉ ትላልቅ የሃይድሮ ኤለክትሪክ ማመንጫ ግንባታዎች፤ በየከተማው ስለተዘረጉ የውሃ መስመሮች፤ የስልክ አገልግሎት ለማዳረስ ስለተወሰዱ እርምጃዎች፤ ስለ ረጃጅም የባቡር መስመሮች ግንባታ እና ስለ አገር አቋራጭ የመንገድ ሥራዎች የሚቀርቡ የተጋነኑ ዘገባዎች ናቸው።
እነዚህ የልማት አውታሮች ግንባታ በአብዛኛው የሚካሄዱት ከምዕራባዊያን መንግሥታት በሚሰጡ የገንዘብ እርዳታና ዕዳው ለልጅ ልጆቻችን በሚተርፍ አለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶች ወለድ እያስከፈሉ በሚሰጡት የረጅም ጊዜ ክፍያ ብድር እንደሆነ ግልጽ ነው።
ወያኔ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 23 አመታት በድህነት ቅነሳና የልማት ማስፋፊያ ስም ከአለም አቀፍ ኅብረተሰብ የተቀበለው የገንዘብ መጠን ሲሰላ ኢትዮጵያ አገራችን እንደ አገር ከተመሰረተችበት ዘመን ጀምሮ በብድርም ሆነ በእርዳታ ስም ይህንን ያህል መጠን ገንዘብ አግኝታ እንደማታውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ ። በዚህም መሠረት ገንዘቡ በአግባብ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አገራችን የትና የት በደርሰች ነበር እያሉ የሚቆጩ የአገሪቱ ልሂቃንና ቅን አሳቢ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም ።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከ3 አመት ገደማ በፊት ይፋ ባደረገው አንድ መረጃ ወያኔ ሥልጣን በተቆጣጠረባቸው የመጀመሪያዎቹ 9 አመታት ብቻ ከ11.5 (አሥራ አንድ ነጥብ አምስት ) ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ ከአገር አሽሽቶ በምዕራባዊያን አገሮች ባንኮች ደብቆአል ። ይህ ከደሃው ጉሮሮ ተቀምቶ በባለሥልጣናቱ የተዘረፈና በህገወጥ መንገድ ከአገር የሸሸው 11.5 ቢሊዮን ዶላር በትክክል ልማት ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ወያኔዎች “ባለ ራዕዩ መሪያቸን” በሚሉት ዘረኛው መለስ ዜናዊ ሥም ለመሰየም ደፋ ቀና የሚሉትን ጅምር “የህዳሴ ግድብ” አይነቱን ሁለት ግዙፍ ግድቦችን በመገንባት የአገሪቷን ገጽታ አበላሽቶ የኖረውን ረሃብ ከምንጩ ማጥፋት ይቻል ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአገሪቱ የሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ “ውሃ የለም፣ መብራት የለም፣ ኔትዎርክ የለም። የሚላስ የሚቀመስ ነገር ማግኘት ተስኖናል፤ ኑሮ ከአቅማችን በላይ ሆኖአል። ትዳር መስርተንና ልጆች ወልደን እያሳደግንበት ካለው የደሃ ጎጆዎቻችን በቀበሌ ካድሬዎች ትዕዛዝ ቤቶቻችን በዶዘር ላያችን ላይ እንዲፈርስ ተደርጎ ሜዳ ላይ ተበትነናል። ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጊዜ ጀምሮ እንገለገልበት ከነበረው የእርሻ ማሳችንና የግጦሽ መሬታችን ተነቅለን ዓይኖቻችን እያዩ ከህንድ፣ ከቻይናና ከአረብ አገር የመጡ ከበርቴዎች መሬታችንን ተቀራምተውታል። አቤት የምንልበት አጣን። ኑሮ መሮናል!!!” የሚሉ እሮሮዎች የወያኔ አፈና የፈጠረውን የፍርሃት ዝምታን ሰብሮ ከአጥናፍ አጥናፍ እየተሰማ ነው።
ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየከረረ የመጣውን የሕዝብ እሮሮ ለማዳመጥ ጆሮ ያልፈጠረበት የዘረኛው ህወሓት አገዛዝ ግን “ነጋ ጠባ የሚደሰኮረው ልማት ምድር ላይ ጠብ አላለልንም፤ መሠረታዊ ችግሮቻችን ከመፍታት ይልቅ እያባባሰ ያለው ምን የሚሉት ልማት ነው?” ብሎ የጠየቀውን ሁሉ “ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሰላም፣ ሽብርተኞ” የሚል ስም እየለጠፈበት ማሰር ማዋከብና ማሳደድ የዘወትር ተግባሩ አድርጎታል።
በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ አለም አቀፍ የሴቶች በዓል ሲከበር ይኸው የሕዝብን ብሶት ባስተጋቡት ወጣት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ የዚህ የወያኔ አፈና እርምጃ ማሳያ ነው። “ብሶት የፈጠረኝ ነኝ” የሚለው ህወሓት፤ ብሶት እሱን ብቻ ፈጥሮ የመከነ ይመስለዋል።
ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ እያካሄድኩ ነው በሚላቸው ትላልቅና ትናንሽ ግንባታዎች መጠነ ሰፊ ብዝበዛና ዘረፋ እያካሄደ መሆኑን የሚያጋልጡ በቂ መረጃዎች አሉት። የወያኔ ልማትና እድገት ማሳያ ተደርጎ ከሚጠቀሱ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ አንስቶ በመላው አገሪቱ ለሚሠሩ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በሙሉ የሚያስፈልጉ የግንባታ ዕቃዎች ስምንቶ፤ አሸዋና ብረታ ብረት የመሳሰሉትን የሚያቀርቡት በባለሥልጣናቱ ንብረትነት የሚታወቁና በቤተሰቦቻቸው ወይም የቅርብ ዘመዶቻቸው ስም የሚተዳደሩ የግል ድርጅቶች ናቸው። የግንባታዎቹን ሥራ ደግሞ የሚያካሂዱት በወያኔ ንብረትነት የሚታወቁ የኢፈርት ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ አይነት ኮንትራት ሰጪ፤ ኮንትራት ተቀባይና ዕቃ አቅራቢ በመሆን በሚበዘበዘውና በሚዘረፈው የሕዝብ ሃብት የወያኔ ሹማምንትና ግብረ አበሮቹ እስከ ልጅ ልጆቻቸው በልተው የማይጨርሱትን ሃብት አግበስብሰዋል።
ይህ አልበቃ ብሎአቸውም አይናቸው ያረፈባቸው ቁልፍ የከተማ ቦታዎች ላይ የሰፈረውን ደሃ ሕዝብ በማፈናቀልና ጎዳና ላይ በመበተን ረጃጅም ፎቆችን እየሰሩ በማከራየት ሥራ ላይ ተጠምደዋል። ከአመታት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች የያዙትን ቦታ ለማስለቀቅ ሆን ተብሎ ንብረታቸው በእሳት እንዲወድም ተደርጎአል። በሕይወት ዘመናቸው ያፈሯት ሃብት በእሳት እንዲጋይባቸው የተደረጉ ዜጎች አቤት የሚሉበት ስላልነበራቸው ሥራ አጥና የጎዳና ተዳዳሪ ለመሆን ተገደዋል። ባለፈው ሁለት ሳምንት ተመሳሳይ እርምጃ ሀረር ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ በተሰማሩት ወገኖቻችን ላይ ደርሶ እንባ ሲራጩ ተመልክተናል።
ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በልማት ስም በወገኖቻችን ላይ የሚፈጽመውን የማፈናቀል ዘመቻ ማስቆም የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው ብሎ ያምናል። ሕዝባችን በጨለማ እየተሰቃዬ ከደጃችን የሚመረት የመብራት ኃይል ወደ ጎረቤት አገር እየተላከ ለማይጠረቃው የወያኔ ሃብት የማጋበስ ጥማት ማርኪያ መሆን ማስቆም የምንችለው እኛው ብቻ ነን። ወገኖቻችን በረሃብ አለንጋ እየረገፉና ነፍሰ አድን የምግብ እርዳታ ከፈረንጅ በምጽዋት እየተቸረን በምድራችን የሚመረት እህል ባህር አቋርጦ ለባለጸጋ አገሮች ገቢያ ሲውል አይተን እንዳላየን ማለፉን ማስቆም የኛ ተግባር ነው። ዕዳው ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ የብድር ገንዘብ በየአመቱ አገር ውስጥ በገፍ እየገባ እናቶችና ህፃናት በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት መሰቃየታቸውን ማስቆም የምንችለው እኛው ነን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በቂ የትምህርት እድልና የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ገንዘብ በሙስናና በሌብነት በተጨማለቁ የአገዛዙ ሹመኞች መዘረፉን ማስቆም ያለብን እኛው ነን።
“ውሃ የለም መብራት የለም ኑሮ ከአቅማችን በላይ ሆኖ መኖር አቅቶናል” የሚለውን የወገን እሮሮ ያሰሙ ልጃገረዶችን ድምጽ መስማት ግዴታችን ነው። የእነዚህ ወጣቶች አርዓያነትን በመቀበል ዛሬውኑ የትግሉን ጎራ በመቀላቀል እብሪተኛውንና ዘረኛውን የወያኔ አገዛዝ ፍጻሜ በማፋጠን ነፃነታችንን እንድንጎናጽፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።

ያልዘሩትን ማጨድ ከቶ አይቻልም! (ግንቦት7)

April 5, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየወያኔ መንግስት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች አጋጭቶ በመካከላቸው ጥርጣሬና መፈራራት አንግሶና የታሪክ ጠባሳዎችን እንደ አዲስ በመጓጐጥ እያደማ ከፋፍሎ ለመግዛት ካለመታከት ያደረጋቸው ሙከራዎች ገና ፍሬ ባያፈሩም ቁጥቋጦዎቹ መብቀል ጀምረዋል። እዚህም እዚያም በካድሬዎች የውስጥ ለውስጥ ተልእኮ የሚለኮሱ እሳቶች መብለጭለጭ ጀምረዋል። ሌላው ቀርቶ በአንድ ብሄረሰብ መሃል ሳይቀር በከባቢ ልዩነቶች ብቻ መናቆሮችና መጋደሎች እያስተዋልን ነው። ሰሞኑን በጉጂና በቦረና ኦሮሞዎች መካከል የወያኔ ሎሌዎች በሚያበረታቱት አተካሮ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ጠፍቷል። ሰዎች ከኑሮአቸው ተፈናቅለዋል። ወያኔ እንደኳስ ጨዋታ ተመልካች ዳር ሆኖ ይመለከታል፣ ያጨብጭባል።
ሰሞኑን ባህርዳር ከተማ ውስጥ በተካሄደ የስፖርት ውድድር ላይ አሳፋሪ ክስተት ነበር። ለሰሚው የሚቀፍ ብልግና የተቀላቀለበት ስድብና ቁርቋሶ አይተናል። ከበስተጀርባ ሆነው ይህንን ለፍቅር ብቻ ሊውል የሚገባ የስፖርት ዝግጅት መርዝ ረጭተውበታል። ከዚህ ላቅ ያሉ የተንኮል ድግሶችም ተደግሰው ህዝብ ውስጥ በወያኔ ከተነዙ የመርዝ ቢልቃቶች ውስጥ ስራ ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል።
ይህ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዘር የሚዘራው ወያኔ ያልተከፋፈለ ህዝብ አይገዛልኝም በሚል ፍልስፍና እንደሆነ በተደጋጋሚ እያየን ነው። ሶማሌ ክልል ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ ፖሊስ በሚል ስያሜ በሚጠሩ የመንግስት ሃይሎች ጥቃት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ የኦሮሞ ማህበረሰብ ከኖረበት መሬት ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጓል። ብዙዎቹ ተገድለዋል። ብዙ ደም መቃበት ተፈጥሯል። በየክልሉ ምስኪን የአማራ ገበሬዎችን መሬት ንብረት በመንጠቅ አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አድርገዋል። መሄጃ የለንም ያሉትንም ቀጥቅጠው እንደገደሏቸው ሰሞኑን ከጅባትና ሜጫ አካባቢ ያሉ መረጃዎችን አይተናል።
እነዚህ በየቦታው የሚብለጨለጩ እሳቶች በዚህ ከቀጠሉ ሁላችንም ወደ ሚያቃጥልና የሚለበልብ የሰደድ እሳት ማደጉ አይቀርም። የወያኔ ባለሟሎች ካለምንም ይሉኝታና ማሰላሰል ይህንን እሳት እያራገቡ ይገኛሉ።
ይህንን አደገኛ አዝማሚያ በንጭጩ ማስወገድ የሚችለው ራሱ ህዝቡና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የነጻነት ሃይሎች ድምጽና ህብረት እንጂ የወያኔ መንግስት አይደለም። ስለዚህ ህዝቡ በተለይም ወጣቶች ከዚህ ወጥመድ ሰብረው እንዲወጡ ግንቦት 7 የነጻነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አጥብቆ ያሳስባል። ተመሳሳይ ተንኮሎችንም ማጋለጡን ይቀጥላል። የብሄርሰብ ልሂቃንም ይህንን መርዝ እንዲቋቋሙ፣ ይልቁንም ወያኔ እንዳይመቸው ይበልጥ መቀራረብና ፈተናውን በጋራ እንድንቋቋም ጥሪያችን በድጋሜ እናቀርባለን።
ያልተዘራ አይታጨድም። ወያኔ የዘራልን መርዝ የሚያፈራው መርዝን እንጂ ሌላ አይደለም። ልዩነቶቻችን እንደዘመኑ በሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በተያዘው መንገድ ማስወገድ አይቻልም።
ዞሮ ዞሮ በዚህ ሳይጣናዊ የወያኔ መሰሪ ሴራ ለምትፈስ ለእያንዳንዶ የደም ጠብታ ተጠያቂው የወያኔ ጉጅሌ መሆኑን አጥብቀን እናሳስባለን። በመሆኑም ለመከፋፈል ከመመቻቸት ይልቅ አንድነታችን በማጥበቅ የነጻነት ሃይሎችን በመቀላቀል ራሳችን እና የሀገራችንን ህልውና ከዚህ ከወያኔ የመከፋፈል መርዝ እንታደግ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Friday, April 4, 2014

Grand public meeting in Oslo Norway 

Our special guest is Mr. Bizuneh Tsge Ginbot 7 executive committee member during the event Discussion on current Ethiopian political situation and the Ethiopian Diaspora roll various programs and food and drinks are ready.
All Ethiopians in Norway are invited Date፥ April 12/2014
Time፥ 15: 00_21:00
Place coming soon

Organized by DCESON
ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ በኦስሎ አፕሪል11/2014

የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ በአፕሪል 11/2014 ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ የጠራ ሲሆን 

የሰላማዊ ሰልፉ አላማ
አምባገነኑ የወያኔ መንግስ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን የስለላ ስራ በመቃወምና
የኖርዌጅያንን የስደተኞች ፖሊሲ በመቃወም ሲሆን

ሰልፉ የሚጀመረው በYoungstorget ልክ 12፥00 ሰዓት ሲሆን ከዛም ወደ ኖርዌጅያን ምክር ቤት/Stortinget/ ሲሆን 14፥00 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል፥፣

የስብሰባው አላማ
የስደተኛ ማህበሩ የሶስት ወር የስራ ሪፖርት
አሁን ያለውን የኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዌይ ችግር እንዴት መፍታት እንደምንችል መወያየት
ጉዳያችንስ በምን አይነት መልኩ ለሚመለከተው ክፍል ማቅረብ እንችላለን

በዝግጅቱም ላይ ለታዳሚዎቹ ምግብ አዘጋጅተናል፥፥The Ark of The New Covenant Healing Minstry ( የአዲስ ቃልኪዳን ታቦት የፈውስ አገልግሎት)

የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ