Sunday, December 1, 2013


‹‹ድኅረ ምርጫ 97 በኢትዮጵያ ያለው ዲሞክራሲያዊ ምህዳር ጠቧል›› አና ጐሜዝ፣ የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባል

ምርጫ 97ን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረትን የምርጫ ታዛቢ ቡድንን የመሩት አና ጐሜዝ ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ በኢትዮጵያ መንግሥትና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ የሰላ ትችትና ወቀሳ በመሰንዘር ይታወቃሉ፡፡ 
ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ በ26ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን፣ ፓስፊክ እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ የፓርላማ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን አና ጐሜዝን በዴሞክራሲ፣ በእስረኞች አያያዝ፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡   
ሪፖርተር፡- ምርጫ 97ን ተከትሎ በእርስዎና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ የማይባል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያቀረቡት የቪዛ ጥያቄ እንዴት ነበር? ቪዛ መስጠት ያለመፈለግ አልያም ሌላ ነገር አጋጥሞዎታል? 
አና ጐሜዝ፡- በፍጹም፡፡ ምንም ዓይነት ክልከላ ወይም እምቢታ አላስተናገድኩም፡፡ ለነገሩ የአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብተት ንኡስ ኮሚቴ ባለፈው ሐምሌ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር እኔም መሄድ እፈልግ እንደሆን ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔም መሄድ ብፈልግም ባልፈልግም ቪዛ አትሰጡኝ ምን ያደርጋል አልኩት፡፡ እርሱ ግን የለም እንሰጥሻለን አለኝ፡፡ እሺ ለአሁን የሥራ ባልደረቦቼ ይጓዙ የእኔ ጊዜው ሲደርስ አመለክታለሁ አልኩ፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአፍሪካ ፓስፊክ ካሪቢያንና የአውሮፓ ኅብረት ጥምር ስብሰባ ላይ ለመካፈል የቪዛ ጥያቄ አቀረብኩ፤ እነርሱም ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ያለምንም ችግር ቪዛውን ሰጥተውኛል፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በማለፋቸው የተለየ የፖለቲካ አተያይ እየተፈጠረ እንደሆነ የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ለማምጣት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ተረድቻለሁ፡፡ በተለይ ሙስናን በመዋጋት የጀመሩት ዕርምጃ ከፍተኛ የሥርዓቱን ባለሥልጣናት ሳይቀር ወደ እስር ቤት አስገብዋል፡፡ ይህም መልካም ጅምር ነው፡፡ 
ነገር ግን በኢትዮጵያ ከፍ ያለ ለውጥ ማየት እሻለሁ፡፡ ይህ የእኔ ብቻ ፍላጐት አይደለም፣ የኢትዮጵያውያንም ጭምር እንጂ፡፡ እዚህ በመምጣቴ ከስብሰባው ጐን ለጐን ሌሎች ሰዎችን በማናገር ለውጡ በእንዴት ያለ ሒደት ላይ እንዳለ ለመመልከትም እሞክራለሁ፡፡ 
ሪፖርተር፡- የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንን በመምራት በ1997 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበሩ የአገሪቱን የምርጫ የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብትንና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ያውቋቸዋል፡፡ አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? 
አና ጐሜዝ፡- እንደሚመስለኝ ድኅረ ምርጫ 97 በኢትዮጵያ ያለው ዲሞክራሲያዊ  ምህዳር ጠቧል፡፡  ከምርጫ 97 በፊት ከነበረበት ገጽታ አንፃር ብሶበታል፡፡ ምርጫውን ተከትሎ እልቂቶችን አይተናል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲታሠሩ አይተናል፣ ለሲቪል ማኅበራት ምህዳሩ ሲጠብ አይተናል፡፡ እንደሚመስለኝ በበጐ አድራጐት ማኅበራት ላይ የወጣው ሕግ አሉታዊ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አላግባብ ጥቅም ላይ ሲውል አስተውለናል፡፡ ሕጉ እጅግ የተለጠጠ ትርጓሜ እየተሰጠው የተለየ ሐሳብ ያላቸውንና የሚቃወሙ ግለሰቦችን ለማጥቃት አገልግሎት ላይ ለማዋል እየሞከረ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የተነሳ ሁኔታው የባሰበት ነው፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም ምርጫ 2002 በቀዘቀዘ ሁኔታ ተከናውኖ አልፏል፡፡ የሥራ ባልደረባዬ ቴስ በርማን ምርጫውን ለመታዘብ በአውሮፓ ኅብረት ተወክሎ ነበር፡፡ ምርጫው መቀዛቀዙን ገልጿል፡፡ ምክንያቱም በምርጫ 97 ኅብረተሰቡ በስፋት ከመሳተፉ በተጨማሪ በምርጫው ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ ይህ ተስፋውም እስከ ድምፅ ቆጠራው ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡም ሆነ እኔ ምርጫው መጭበርበሩን ተረድተናል፡፡ ስለዚህ በምርጫ 2002 ኅብረተሰቡ በአብዛኛው ወደ ምርጫ አልሄደም፡፡ እኩለ ቀን ላይ ሁሉም ነገር የተጠናቀቀበት የምርጫ ጣቢያዎች ነበሩ፡፡ 
የአውሮፓ ኅብረትን የወከለው ቴስ በርማን የምርጫውን ሪፖርት ለማቅረብ እንኳን ወደ አዲስ አበባ መመለስ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ሪፖርቱ ሒስን የያዘ ስለሚሆን ነው፡፡ ሒሱ ግን ገንቢ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህን ከልብ የመነጨና ቀና ሒስ መቀበል አልፈለጉም፡፡ 
እንደሚመስለኝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፉ በኋላ ነገሮች በሚገርም ሁኔታ ተለውጠዋል፤ የሚለወጡም ይመስለኛል፡፡ ይህም የመነጨው አመራሩ በመለወጡ ነው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ለማምጣት እየሠሩ ይመስለኛል፡፡ ነገሮች ተጠናክረው እንዲጓዙ እንፈልጋለን፡፡ በፀረ ሙስና ላይ የተጀመረው ትግል፣ የዲሞክራሲያዊ ምህዳሮች መስፋፋት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች እንዲስፋፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ማየትን እንሻለን፡፡ 
እርግጥ ነው በተደጋጋሚ በመንግሥት በኩል የሚነገር መከራከሪያ አለ፡፡ ይህም እነዚህ ግለሰቦች የታሰሩት ጋዜጠኞች በመሆናቸው ሳይሆን በሽብርተኝነት ወንጀል ነው ይላል፡፡ እኔ ግን ይህን አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም አሁን አሁን ሽብርተኝነት የሚለው ሐሳብ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ዝም ለማሰኘት እያዋሉት ነው፡፡ 
ከአሁን በፊት በአገሬ የነበረው አምባገነን መንግሥት ይጠቀምበት የነበረው ቃል አመፀኛ የሚል ነበር፤ አሁን ግን ቃሉ ሽብርተኛ ሆኗል፡፡ እንደሰማሁት እነዚህ ሽብርተኛ የተባሉ ግለሰቦች ያለፉበት የፍትሕ ሥርዓቱ ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ ግለሰቦቹ የሽብር እንቅስቃሴን ማድረጋቸው የሚያስረዳ በቂ መረጃ አልቀረበም፡፡ ለኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ጥሪ ማስተላለፍ ፈጽሞ የሽብር ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ የትኛውም ዲሞክራሲ ሊጠብቀው የሚገባ እውነተኛ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ድኅረ ምርጫ 97 ኢትዮጵያን አሁን ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል? 
አና ጐሜዝ፡- አዲስ አበባ የቆየሁት ከመጋቢት ጀምሮ እስከ ምርጫው ድረስ እንደሆነ ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጥቂት ተስፋ ሰጪ ነገሮች ነበሩ፡፡ መንግሥት በተወሰነ መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩን ክፍት ለማድረግ ይሞክር ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የብዙኃኑን ሐሳብ ተቆጣጥሮት የነበረው ለአምስት ጊዜያት በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈው የፓርቲዎችን ክርክር ነው፡፡ ይህ ክርክር የሕዝቡን ሐሳብ ተቆጣጥሮት የነበረ ሲሆን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያንን በመፍቀዳቸው እንደ ተጸጸቱ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ አማራጮችን በአግባቡ የተረዳበት ክርክር ነበርና፡፡ 
ድኅረ ምርጫ የተፈጠረውን ሁኔታም አስታውሳለሁ፣ በምርጫው ዕለት ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለምንም በቂ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ፡፡ ይህም ምን ያህል እንደ ተሸበሩ የሚያሳይ ነበር፡፡ ምርጫው በአጠቃላይ በሰላምና በሥርዓት ተካሂዷል ብሎ የሚያምን ከሆነ እንዲህ ያለ ውሳኔ ለምን አስፈለገ? ለምን ሕዝቡን አያማክሩም ነበር፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፣ ምርጫውን ለማጭበርበር በመታሰቡ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መሠረት አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ የማወዳድረው ከቅድመ 97 ሁኔታ ጋር ነው፡፡ በዚያን ወቅት ቢያንስ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ነበራቸው፡፡ አሁን ግን በፓርላማው መቀመጫ ያለው ተቃዋሚ አንድ ብቻ ነው፡፡ 
እርግጥ ነው አንዳንድ የማውቃቸው ግለሰቦች የሚዲያው ዘርፍ በትንሹም ቢሆን እየተከፈተ እንደሆነ ገልጸውልኛል፡፡ ነገር ግን እየተከፈተ ያለው የሚዲያው ዘርፍ ዋናው ሳይሆን አማራጭ የሆኑት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ እርሱም የሚመነጨው ደግሞ ሕዝቦች ከቴክኖሎጂ ጋር ባላቸው ቅርርብም ጭምር ነው፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የቴክኖሎጂ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን ያለውን ቴክኖሎጂ ለማገድ ከአውሮፓም ይሁን ከእስራኤል የምታመጣው ባለሙያ ለመቆጣጠር የሚሆንለት አይሆንም፡፡ በምትቀጥራቸው ባለሙያዎች ፌስቡክንም ሆነ ትዊተርን መቆጣጠር እጅግ አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ የተነሳ ባለሥልጣናቱም ወደ እዚያው ለመቅረብ እየሠሩ ይመስለኛል ምክንያቱም መንግሥት ሚዲያውን በሥነ ሥርዓት ካልከፈተው ሕዝቡ የራሱን መንገድ ይፈልጋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ዲሞክራሲን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን እንዲሁም ስለ እስረኞች ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል?
አና ጐሜዝ፡- አዎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት አባዱላ ገመዳ ምሳ ጋብዘውኝ ነበር፡፡ ከእርሳቸውም ጋር አቶ ተሾመ ቶጋ ነበሩ [የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ፣ በአሁን ሰዓት በብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር] ከእነዚህ ባለሥልጣናት ጋር በጣም ግልጽ የሆነ ውይይት ከማድረጋችን በተጨማሪ በግልጽ ያሉኝን ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎችና ሒሶች ሰንዝሬያለሁ፡፡ ምንም ግለሰባዊ ችግር እንደ ሌለብኝም አስረድቻለሁ፡፡ በግሌ የማገኘው ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌላ ጥቅም የለኝም፤ ሥራዬን ግን በቁርጠኝነትና በትጋት እሠራለሁ፡፡ ስለዚህም ያየሁትንና የሰማሁትን የመናገር ግዴታ አለብኝ፡፡ በዚህም መሠረት ውይይታችን እጅግ በጣም ግልጽና ገንቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከባለሥልጣናቱ ያገኙት መልስ ምን ይመስላል? 
አና ጐሜዝ፡- ይህን እንኳን በዝርዝር አልነግርህም፡፡ የውይይታችን አንዱ ጠቀሜታም በግል መያዙ ነው፤ ምክንያቱም ውይይታችን የተካሄደው በግል ስለነበር፡፡ ነገር ግን ላረጋግጥልህ የምፈልገው ነገር ቢኖር ውይይታችን የፖለቲካ ምህዳሩን ስለማስፋት፣ የታሠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ስለማስፈታት፣ ለበጐ አድራጐት ማኅበራት ምቹ ሁኔታን ስለመስጠትና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማጠናከርና መሰል ጉዳዮች የተዳሰሱበት ከመሆኑም በተጨማሪ ግልጽና ገንቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከባለሥልጣናቱ ባገኙት መልስ ረክተዋል? 
አና ጐሜዝ፡- እንደሚመስለኝ እኔን ለመስማት መፍቀዳቸውና መወያየታችን አንድ ጥሩ ምልክት አድርጌ እመለከተዋለሁ፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በሙሉ የኢትዮጵያ ጉዳዮችና ሒደቶች ናቸው፡፡ የትኛውም አካል ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ማሳደር አይችልም፡፡ ነገር ግን ከእኔ ጋር ለመወያየትና እኔን ለመስማት መፍቀዳቸው እንደ ጥሩ ጐን አድርጌ እመለከተዋለሁ፡፡ 
ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከሚወቅሱበት ጉዳይ አንዱና ዋነኛው የእስረኞች ሁኔታ ነው፡፡ እዚህ በመጡበት ወቅት ወደ ቃሊቲ ተጉዘው እስረኞችን ለመጠየቅ ጥያቄ አቅርበዋል?
አና ጐሜዝ፡- ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ ጥያቄዬ ግን በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን የጋራ ስብሰባው የፖለቲካ ኮሚቴ ወደ ስፍራው ተጉዞ እስረኞችን እንዲጐበኝ ባለፈው ቅዳሜ ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ (ይህ ኢንተርቪው የተካሄደው ሰኞ ዕለት የነበረ ሲሆን ረቡዕ ዕለት በሌዊ ሚሽል የተመራ ቡድን እስረኞችን ጐብኝቷል) 
ከእስረኞች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚደመጥ ነገር አለ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የታሰሩት ጋዜጠኛ ወይም ሌላ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቅስ አሸባሪ በመሆናቸው ነው የሚለውን አስተሳሰብ የሚጋሩ የአውሮፓ ተወካዮችም እንዳሉ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ እኔ ግን በዚህ አስተያየት ፈጸሞ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም የስዊድን ዜግነት ያላቸው ሁለት ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ተከሰው መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበርካታ ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባትና ተፈርዶባት መፈታቷ ይታወሳል፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጉዳይም የተለየ አይደለም፡፡ የታሰሩት ግለሰቦች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምልክቶች ናቸው፡፡ የወጣቱ ትውልድ ምልክቶች ናቸው፤ ምናልባትም ያቋቋሙት የፖለቲካ ሥርዓትም የላቸውም፡፡ 
ሪፖርተር፡- መንግሥት በሽብርተኝነት ነው ያሰርኳቸው የሚለውን የሚያምኑ ከሆነና እነዚህ ሰዎች አሸባሪ አይደሉም ብለው የሚያስቡ ከሆነ የእርስዎን ሐሳብ የሚያጠናክር ምን መረጃ አለዎት? 
አና ጐሜዝ፡- ኢትዮጵያ ከሽብርተኝነት ጥቃት ሥጋት ነፃ ነች እያልኩ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያና የአውሮፓ አገሮች ከሽብርተኝነት ጥቃት ሥጋት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ነገር ግን በስመ ሽብርተኝነት የዲሞክራሲ ምህዳሩን ማጥበብ፣ የተለየ ሐሳብ ያላቸውንና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን የሚጠይቁ ግለሰቦችን ፀጥ ማሰኘት፣ ሽብርተኝነትን መታገል አይደለም፡፡ ይህ እንዲያውም ግለሰቦችን በይበልጥ ወደ ሽብር ተግባር እንዲሰማሩ መመልመል ነው፡፡ 
በኢትዮጵያ ያለውን የሽብር ሥጋት ደረጃ ለማሳነስ እየሞከርኩኝ አይደለም፤ ነገር ግን የታሳሪዎቹን የፍርድ ሒደት የታዘቡ ግለሰቦች እንደነገሩኝ የፍርድ ሒደቱ ፍትሐዊ ካለመሆኑም በተጨማሪ የቀረቡት ማስረጃዎች የግለሰቦቹን የሽብርተኝነት ተግባር የሚያሳዩ አልነበሩም፡፡ ለዚህ ነው እነዚህ ሰዎችን አሸባሪ ብሎ መጥራትን የማልቀበለው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ይህ የሰጡኝ ማብራሪያ ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጥ ሁነኛ ትንታኔ ሊሰጡኝ ይችላሉ? 
አና ጐሜዝ፡- አላውቅም፡፡ እኔ እኮ ታሳሪዎቹን በግል አላውቃቸውም፡፡ ለምሳሌ የብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይን ያነሳህ እንደሆነ በግል እንተዋወቃለን፡፡ እንዲሁም ከብርሃኑ ነጋ ጋር የግል ትውውቅ አለን፡፡ እነዚህ እስረኞች ግን በግሌ አላውቃቸውም፡፡ 
ሪፖርተር፡- በቅርበት እንደሚያውቋቸው ከገለጹት ግለሰቦች መካከል አንዱ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው፤ እርሳቸው ያቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አሸባሪ ይቆጠራል፡፡ እሳቸውም ሥርዓቱን ለመለወጥ ከምርጫ የተለየ መንገድ ያስፈልጋል እያሉ ነው፡፡ እርሳቸው አቅጣጫቸውን ይቀይራሉ ብለው አስበው ያውቃሉ?
አና ጐሜዝ፡- ብርሃኑ ነጋን የማውቀው በምርጫ 97 ወቅት ነው፡፡ ቅድም የገለጽኩት በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቃዋሚ ጐራ ወኪል እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በክርክሩ የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቃዋሚ ጐራውን በመወከል ስሙ የሚነሳ ግለሰብ ቢኖር ብርሃኑ ነጋ ነበር፡፡ እርግጥ ነው በየምርጫ ወረዳቸው የታወቁ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳና ወዘተ፡፡ በነገራችን ላይ ብርሃኑ ነጋ በምርጫ 97 ወቅት ባይታሰር ኖሮ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ይሆን ነበር፡፡ ከእስር እንደተፈታም ወደ ስደት አመራ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች አቅጣጫውን እንዲቀይር ያደረጉት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአገሪቷ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ሚና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓት በመበላሸቱ የተለወጠ ይመስለኛል፡፡ 
ሪፖርተር፡- እርስዎ በስፋት የሚታወቁት የኢትዮጵያ መንግሥትንና የአውሮፓ ኅብረትን ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፋፋት ጋር ባለባቸው ችግር በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ነው፡፡ አሁን በእርስዎ ላይ የተፈጠረ የአቋም ለውጥ አለ? 
አና ጐሜዝ፡- ኢትዮጵያን በተመለከተ ከፍተኛ ትችትና ሒስ እሰነዝራለሁ፡፡ አውሮፓ ኅብረት ላይ የምሰነዝረው ሒስ ደግሞ የባሰ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረትን በተለያዩ ጉዳዮች እተቻለሁ፡፡ በተለይ በኅብረቱና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ትችት እሰነዝራለሁ፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ ከፍተኛና ጠንካራ ተፅዕኖ ማሳረፍ ሲችልና በኢትዮጵያ ጉዳይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ሲችል ዝምታን ይመርጣል፡፡ ይህን አይቻለሁ፡፡ 
አንዳንድ ሰዎች የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ የተሻለ እንደሆነ ይገልጹልኛል፡፡ እርሱን እጠቀምበታለሁ፤ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውልም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ጫና የማሳደር ዲፕሎማሲ (ሜጋፎን) መጠቀም ይኖርብናል፡፡ 
ባልደረባዬ ሊዊ ሚሸል ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሁለት የስዊድን ዜግነት ያላቸውን ጋዜጠኞችን አስፈትቶ ስለ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ጉዳይ አንዳች ሳይሠራ ወደ አውሮፓ በመመለሱ በጣም ተናድጄ ነበር፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያውያንና በአጠቃላይ ለአፍሪካውያን የምናስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? እኛ የምንጨነቀው ለዜጐቻችን ብቻ ነው፡፡ ይህ ተግባር ተራና ማዳላት ያለበት ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- በአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ በነበሩበት ወቅት ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንደነበሮት ይታወሳል፤ እዚህ ከመጡ ያገኟቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አሉ?
አና ጐሜዝ፡- እስከ አሁን ያገኘሁት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የለም፡፡ ነገር ግን እንደማገኛቸውም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የትውልድ ችግር አለ፡፡ በግሌ በተቃዋሚ ፓርቲና በውጪ አገሮች ባሉ ኃይላት መካከል ግንኙነት ቢፈጠር መልካም ይመስለኛል፡፡ ይህም ለፖለቲካው ምህዳር መከፈትና ለውይይት መዳበር ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ እውነተኛ ለሆነ የዲሞክራሲ ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ መጠላላትን አስወግዶ ወደ ፊት ለመጓዝ ይረዳል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ምርጫ 97ን ተከትሎ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተደጋጋሚ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዴት ይገልጿቸዋል? 
አና ጐሜዝ፡- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እስከ ምርጫው ድረስ የነበረኝ ግንኙነት መልካም የሚባል ነበር፡፡ ከእርሳቸው ጋር ግልጽ የሆኑ ብዙ ውይይቶች አካሂደናል፡፡ ተለዋዋጭ ባሕሪ እንዳላቸው ለመታዘብ ችዬ ነበር፡፡ በግንኙነታችን መጀመሪያ አካባቢ አምናቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ሊያሞኙኝ እየሞከሩ እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እርሳቸው በጣም ክፉ ነበሩ፡፡ በጣም ክፉ የሆነ አእምሮ የነበራቸው ናቸው፡፡ ብልህ ናቸው ግን ክፉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ላይ የጻፉትን የምንጊዜውም ረዥሙን ርእሰ አንቀጽ አልረሳውም፡፡ መጨረሻ ላይ ግለሰባዊ ጥቃት በመሰንዘር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንዘብ ተቀብላለች የሚል ዘመቻ ጀመሩ፡፡ ፈጽሞ ተራ የፈጠራ ውሸት ነው፡፡ 
እኔ በግሌ ከእርሳቸው ጋር ምንም ዓይነት ችግርም፣ ጸብም ባይኖረኝም እኔን በመክሰስና በመዝለፍ ጉዳዩን ግለሰባዊ አደረጉት፡፡ እርግጥ ነው ያኔ በጣም በጣም ብናደድባቸውም አሁን ግን የሉም፤ ሄደዋል፡፡

No comments:

Post a Comment