Sunday, August 4, 2013

ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ሳንገል እየሞትን እናስከብራለን! አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

August 4, 2013
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም በጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቆ ወደ ንቅናቄው ከገባ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ህዝባዊ ድጋፍና በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት እና የነፃነት ጥያቄ ድምፅ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡
በአንፃሩ ገዥው ፓርቲ የህዝቡን የነፃነት ድምፅ ለማፈን ንቅናቄያአችንን ከጀመርን እለት ጀምሮ በርካታ መሰናክሎችን እየፈፀመ ይገኛል፡፡
በጎንደርና በደሴ ያደረግነውን ሰላማዊ ሰልፍ በተደራጀ መንግስታዊ ሽብር ለማደናቀፍ የተሞከረውን ሙከራ በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ ከሽፎ የህዝቡን የነፃነት ድምፅ ማሰማታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይህንን የነፃነት ድምፅ በሌሎች ከተሞች ተቀጣጥሎ እንዳይዘልቅ ከሼክ ኑር ኢማም አሟሟት ጋር በማያያዝ ገዢው ፓርቲ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ በተለያዩ ከተሞች ህዝቡን በማስገደድ አንድነት ፓርቲን እንዲያወግዝ በየቀኑ ሰልፍ በማስወጣት ላይ ይገኛል፡፡Unity for Democracy and Justice (UDJ) party
ሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በጂንካ ፣ ወላይታ ፣ ባህርዳር ፣ አርባምንጭ እና መቀሌ ሰላማዊ ሠልፍ እና ህዝባዊ ስብሰባ እናደርጋለን ብሎ አንድነት ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው በሚገኙ አባሎቻችን ላይ ማዋከብና ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ሐምሌ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ወላይታ ለቅስቀሳ የገባው የአዲስ አበባ ልዑክ በአካባቢው ባለስልጣኖች  መንግስታዊ ውንብድና ተፈፅሞበታል፡፡ ታርጋ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በብዛት በማሰማራት ለቅስቀሳ በተንቀሳቀሱ አባሎቻችን ይዘው የወጡትን በራሪ የቅስቀሳ ወረቀቶችንና የፀረሽብር ህጉን ለማሰረዝ የተሰባሰቡ ፊርማዎችን ከእጃቸው ላይ ነጥቀዋቸዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም ዘራፊዎችን ለማስቆም ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ለቅስቀሳ የተሰማራውንም መኪና አራቱንም ጎማ በማተንፈስና ሹፌሩን በመደብደብ ከተማውን ለቆ እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ፡፡ በድምፅ ማጉያ መሳሪያም  ቅስቀሳ እንዳናደርግ ተከልክለናል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የወላይታ የዞን አመራር አባል የሆነችው  ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ ከትላንት ሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓ.ም እለት ጀምሮ በግፍ ታስራ ትገኛለች፡፡ በእስር ቤትም የማታምንበትን ሰነድ እንድትፈርም መገደድዋን ለማወቅ ችለናል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ህዝበ ሙስሊሙን ለአመፅ እንደሚያነሳሳ አድርገው ያቀረቡትን ሰነድ አልፈርምም ፓርቲዬም ይህንን አልፈፀመም በማለት ፓርቲውን ለመወንጀል በተዘጋጀው የሀሰት ሰነድ ላይ ሳትፈርም ቀርታለች፡፡ በአጠቃላይ የመንግስት የፀጥታ ኃላፊዎች እና የአስተዳድር ኃላፊዎች የህገ-መንግስት ጥሰት በአንድነት ፓርቲ ላይ ፈፅመዋል፡፡ በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ላይ ሆነንም በወላይታ ህዝባዊ ስብሰባውን በነገው ዕለት ሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በተያዘለት እቅድ መሰረት በህዝባችን ድጋፍ ይከናወናል፡፡
በጂንካ ፣ በአርባምንጭ እና በባህርዳር  ቅስቀሳው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን  ህዝቡም  ድጋፉን በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ በተለይም በባህርዳር የባጃጅ ሹፌሮች በግል ተነሳሽነት የቅስቀሳው አካል በመሆናቸው የባህርዳርን ህዝባዊ ሰልፍ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
በአንፃሩ በመቀሌ ከተማ ከሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ቅስቀሳ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ የሰነበተው ልዑክ ምንም ዓይነት የድምፅ ማጉያ መሣሪያ እንዳይጠቀም ከመታገዱም በላይ ለቅስቀሳ ያዘጋጀውን ሞንታርቮ በአደባባይ በፖሊስ ተቀምቷል፡፡ በቅስቀሳ ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ብ/ም/ቤት አባል አቶ እንግዳ ወ/ፃዲቅ እንዲሁም የትግራይ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ክብሮም ብርሃነ እና አቶ አርአያ ፀጋይ በቀዳማይ ወያኔ ፖሊስ ጣቢያ በአሁኑ ሰአት በዕስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን በደል በተቀነባበረ መልኩ እየፈፀሙ ያሉት የከተማው አስተዳደር እና የፀጥታ ዘርፍ ክፍሉ በጋራ ሲሆኑ ህገ-መንግስቱን በጉልበት በመናድ በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳናደርግ በኃይል አደናቅፎናል፡፡ ይህንን የህገ-መንግስት ጥሰት አንድነት ፓርቲ በፍፁም በዝምታ አይመለከተውም፡፡ የጀመርነውን ሠላማዊ ትግል አጠናክረን ከሰፊው የትግራይ ህዝብ ጋር በመሆን እንቀጥላለን በቅርብ ቀን በድጋሚ በመቀሌ ከተማ ሠላማዊ ሰልፍ የምንጠራ መሆናችንን እያሳወቅን ገዢው ፓርቲ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በግፍ ያሰራቸውን የፓርቲያችንን አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡ የመቀሌ ነዋሪዎች መንግስት በአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የፈፀመውን አፈና ፊት ለፊት በመቃወም ያሳዩትን አጋርነት ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ አንድነት ፓርቲ ሳይገድል እየሞተ ህገ-መንግስቱን የማስከበር ትግሉን አጠንክሮ ዛሬም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
መንግስት ህገ-መንግስቱን ያክብር!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment