Sunday, April 21, 2013

Home » ዜናዎች... » ኢህአዲግ (ወያኔ) የአባይን ግድብ የቦንድ ሽያጭ በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መተንኮሻ አድርጎታል

ኢህአዲግ (ወያኔ) የአባይን ግድብ የቦንድ ሽያጭ በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መተንኮሻ አድርጎታል

GUDAYACHN BLOG
ዛሬ እነሆ በኖርዌይ እንዲህ ሆነ
Ethiopians in Norway protest, April 2013
ከኖርዌይ ከተሞች ውስጥ በደቡባዊ ክፍል የምትገኘው ስታቫንገር ከተማ ዛሬ ሚያዝያ 12/2005 ዓም በስዊድን የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ መብራት በተገኙበት ለአባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ የተዘጋጀው ዝግጅት ከኦስሎ ከ ስምንት ሰዓታት በላይ በአውቶቡስ ተጉዘው በስብሰባው በተገኙ ኢትዮጵያውያን በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ዝግጅቱ ተሰርዞ አምባሳደሯ በፖሊስ ቦታውን ለቀው  እንዲሄዱ ተመክረው አዳራሹን ለቀው ወጥተዋል።
በመርሃግብሩ መክፈቻ ላይ በሥርዓት ተቀምጠው የተገኙት ኢትዮጵያውያን መርሃግብሩ ከመጀመሩ በፊት ”በዘመነ ኢህአዲግ የተገድሉትን ኢትዮጵያውያን በቅድሚያ በህሊና ፀሎት እናስብ ይህንንም ለማድረግ ሁላችንም ከተቀመጥንበት እንነሳ” በማለት አምባሳደሯም እንዲነሱ እና አብረው በፀሎት እንዲያስቡ ይጠይቃሉ።አምባሳደሯም ሆኑ አብረዋቸው የመጡት ፈቃደኛ አልሆኑም። በመቀጠል ኢትዮጵያውያኑ እንግዲያው ስለ አባይግድብ አሁን ልንነጋገር አንችልም በማለት ያስታውቃሉ።በእዚህ መሃል ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፅ መሰማት ይጀምራል።
”ከአባይ በፊት የሰብአዊ መብት ጥሰት ይገደብ!”
”የሙስሊሙ ድምፅ ይሰማ!”
”የኢትዮጵያውያን ድምፅ ይሰማ!”
”የዘር መድሎ ይቁም!” (stop apartheid in Ethiopia!” ወዘተ… የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ላይ ሳሉ የኖርዌይ ፖሊስ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሁሉም እንዲቀመጡ ይነገራቸዋል። በእዚህን ጊዜ ግን ኢትዮጵያውያኑ የኮኮብ ምልክት ያለበትን ከአምባሳደሯ ጀርባ ባለው ግድግዳ ላይ የተለጠፈውን ባንዲራ የኢህአዲግ አርማ ኮኮብ በሌለበት በኢትዮጵያ ባንዲራ ሸፍነው ጨርሰው ነበር።
Ethiopians in Norway raised Ethiopian flag
ፖሊሱ ኢትዮጵያውያንን ካስቀመጠ በኃላ ቀጥሎም ሁኔታው ደህና መሆኑን ለማስረዳት ይሞክራል። በእዚህ መሃል ኢትዮጵያውያኑ ይብሱን  ቁጣቸውን በዜማ ይቀጥላሉ።
”ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም የደፈረሽ ይውደም”
ይህን የተመለከቱት ፖሊሶች ኢትዮጵያውያኑን ከማስወጣት አምባሳደሯን ማስወጣት ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ ስለተረዱ አንዱ ፖሊስ ወደ አምባሳደሯ ቀርቦ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ በቃልም በእጁም መውጣት እንዴት እንደሆነ እያሳየ ይነገራቸውል። አምባሳደር መብራት ቦርሳቸውን አንስተው ወደ አዳራሹ ዘወር እያሉ እየተመለከቱ ወደ በሩ አዘገሙ። ኢትዮጵያውያኑ ቀጠሉ።
”ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም የደፈረሽ ይውደም”’
”ሌባ ሌባ አለ ገና አለ ገና!”
አምባሳደሯ ፈጠን ባለ እርምጃ በፖሊስ ታጅበው ወደ መኪናቸው ሄዱ።
ኢህአዲግ የአባይን ግድብ የቦንድ ሽያጭ በባህር ማዶ የሚኖሩ  ኢትዮጵያውያንን መተንኮሻአድርጎታል።
ማንም ኢትዮጵያዊ አባይ ቢገደብ ኢትዮጵያ ከድህነት ብትወጣ አይጠላም። ዛሬም  ተቃውሟቸውን የገለፁት ኢትይጵያውያን ለኢትዮጵያ ሞት የሚመኙ ሆነው አይድለም። ኢህአዲግ ግን በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ያሳጣ እየመሰለው ብዙ ተቃዋሚ አለ ብሎ የሚያስበበት ቦታ ሁሉ የአባይ ግድብ ቦንድን ካርድ እየመዘዘ የልዩነት መስመር በኢትዮጵያውያን መሃከል ይፈጠራል ብሎ ያስባል። ለእዚህም አይነተኛ ማስረጃው የመጀመርያው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ዝግጅት በዋሽግተን ዲሲ  ሲዘጋጅ ብዙ ኢትዮጵያውያን ካርድ ወስደው አክትቪስት ታማኝ በየነን ጨምሮ ወደ ስብሰባው ቦታ ሲሄዱ ”የእንጀራ ልጅ እና የቤት ልጅ” በሚል መለያ አድርጎት ”አንተ አትገባም አንተ ግባ” እያለ መለየት ጀመረ።
”በሀገራችን ጉዳይ ያለንን ሃሳብ መስጠት እንፈልጋለን ካርድ ይዘናል” ያሉ ታማኝንም ጨምሮ  እንዳይገቡ ተከለከሉ።
በወቅቱ የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ሃሳብ ቢኖራቸው ሃሳባቸውን መስማት እና ምላሽ መስጠት ያን ቀን መግባባት ባይቻል ለቀጣይ ሌላ ስብሰባ አድርጎ መመካከር የጤነኛ መንግስት ልዑክ አሰራር ነበር።ኢህአዲግ ግን ከመጀመርያው የአባይ ግድብን ሲያነሳ በባህርማዶ ያለው ሕዝብ ሲቃወም በሀገር በት ያለው መደገፉ ስለማይቀር ይለያያል። በውጭ ያለውም ብሔራዊ ስሜቱ አይሎ እርስ በርሱ ይከራከራርል የሚል ታሳቢ ያደርገ አቀራረብ ስለነበረው በዋሽግተኑ ስብስባ ላይ እራሱ ኤምባሲው በድብዳቤ የጠራቸውን ሁሉ ተምታተውበት አላስገባም አለ።ኢትዮጵያውያን በገዛ የሀገራቸው ጉዳይ ባይተዋር ሆኑ።
በእንደዚህ አይነት የተጀመረው የ አባይ ጉዳይ ይሄው ኢህአዲግ እስካሁን ድረስ እንደማስይሳካ እያወቀ በባህር ማዶ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች እና የሀገራቸው ጉዳይ የእግር እሳት የሆነባቸውን ኢትዮጵያውይንን መተንኮሻ አድርጎ ይጠቀምበታል።በነገራችን ላይ ይሄው ተመሳሳይ መርሃግብር በኦስሎ ለ አፕሪል 23/2013 መርሃግብር መያዙን ከአምባሲው ድህረገፅ ላይ የተለጠፈው ማስታወቂያ ያስነብባል። ሃገራዊ ህብረት ሳይፈጠር፣ዜጎች ከአንድ ክልል ወደ አንድክልል ካልፈቃድ ለምን ገባችሁ ተብለው እየታሰሩ(የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በ ቤንሻንጉል ክልል ለመታሰር ያበቃቸው)፣ በሺዎች መሬት እና ንብረታቸውን ተነጥቀው ሲንከራተቱ አንዳች ያልተናገረው መንግስት ይህም ከፍተኛ ተቃውሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በፈጠረበት በእዚህ ጊዜ ስለ አባይ ግድብ ቦንድ ግዙ ብሎ መጠየቅን ምን ስም እንስጠው?
ጌታችው
ኦስሎ

Tuesday, April 16, 2013


“አማራንና አማርኛን ማጥፋት የህወሃት ፕሮግራም ነው”

evicted
አማርኛ ተናጋሪዎችን የማመናመን፣ የማደህየት፣ የማራቆትና ክልላቸውን እያሳነሱ የማጥፋት እቅድ በህወሃት መርሃግብር ውስጥ የተካተተ ዋና ተግባር እንደሆነ ተገለጸ። አማርኛ ቋንቋንም ማሽመድመድ የዚሁ እቅድ አካል መሆኑ ተዘግቧል።
አቶ ገ/መድህን አርአያ ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ በህወሃት ፕሮግራም ገጽ 18 አካባቢ “አማራ የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ጠላት እንደሆነ ተመልክቷል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም አማራ ማጥፋት የቅስቀሳው ዋና መሳሪያ ቢሆንም የትግራይ ህዝብ አልተቀበለም ብለዋል። ቅስቀሳውን አንቀበልም ያሉ “የትግራይ ሸዋ” ተብለው መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል።
በተለይ የድርጊቱ ዋና አስተባባሪ በማለት የጠቀሷቸው አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ስብሃት፣ አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ አባይ ጸሐዬን የጠቀሱት አቶ ገ/መድህን፣ በ1972 በሰሜን ጎንደር የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን አጋልጠዋል። በወቅቱ የተካሄደው ጭፍጨፋ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነም አመልክተዋል። “በሰላም እጃቸውን የሚሰጡ ወታደሮች እንኳ አማርኛ የሚናገሩ ከሆነ ይረሸኑ ነበር” ሲሉ እነ መለስ ያለቸውን በዘር ላይ የተመሰረተ ቆሻሻ አመለካከት አጋልጠዋል።
“ኢትዮጵያ የምትበተነው አማራ ሲጠፋ ነው” በሚለው የነመለስ ሃሳብ መተግበር የጀመረው ህወሃት አዲስ አበባ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑንን ያወሱት አቶ ገ/መድህን፣ ህወሃት ያሰማራቸው ከ350ሺህ በላይ ካድሬዎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ አማራዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንዲጨፈጨፉ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ብአዴንን “አማራን ለማጥፋት የተፈጠረ፣ ጸረ አማራ ድርጀት” ሲሉ የሰየሙት አቶ ገ/መድህን፣ አመራሮቹ የኤርትራና የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን በርግጠኛነት ተናግረዋል። የትግራይ ህዝብ የተወከለው “በባንዳ ልጆችና የኤርትራ ተወላጆች ነው” ሲሉም ህዝቡ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱን “የባሻ ወልዱ ልጅ ነው” በማለት የትግራይ ህዝብ በባንዳ ኤርትራዊ ልጅ እንደሚመራ ያመለከቱት አቶ ገ/መድህን፤ ብርሀነ ገብረክርስቶስ፣ ቴድሮስ ሃጎስ፣ ቴድሮስ አድሃኖም፣ በማለት በመዘርዘር የባንዳ ልጆች መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።
“አማራው የሚኖርበትን መሬት በመውሰድ መሬቱን ያጠቡበታል፣ ከሌላው ክልል በማባረር የሚኖርበትን ክልል ያጠቡታል” ያሉት አቶ ገ/መድህን፣ ይህ የሚደረገው ከመጀመሪያው እንዲጠፋ የተወሰነበትን ህዝብ አጥብቦ በማፈን በችግር ለመግረፍና ለመቆጣጠር ተብሎ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘር የማጥራት የህወሃት የቀደመ ድርጅታዊ መዋቅር እንደሆነ በማመልከት መለስን የጠቀሱት አቶ ገ/መድህን፣ “አማራውን ዝም ካልነው አያስቀምጠንም” የሚለው የመለስ መፈክር አካል የሆነው የቤኒሻንጉል ክልል ርምጃ የህወሃት ቤት ስራ እንደሆነ አረጋግጠዋል። አማራውን ፋታ ማሳጣት፣ ማንገላታት፣ ስነልቦናውን መግፈፍ ህወሃት በፕሮግራም ደረጃ የያዘው እቅድ ስለሆነ ወደፊትም እንደሚቀጥል አቶ ገ/መድህን ተናግረዋል።
“ሞት መፍራት አያስፈልግም። የተቀደሰ ሞት መሞት ክብር ነው” ሲሉ በቃለ ምልልሳቸው መጨረሻ የተናገሩት የቀድሞው የህወሃት የፋይናንስ ሃላፊ ህዝቡ ተባብሮ ህወሃትን ማስወገድ ካልቻለ ማፈናቀሉና መሰደዱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስጠንቅቀዋል።

Thursday, April 11, 2013

ወያኔ የምረጡኝ ቃለ መሃላ እያስፈጸመ መሆኑ ተሰማ፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ቃለ ማህላ ፈጸሙ

ትናንትናው እለት በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሴቶች  በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ኢህአዴግን እንመርጣለን የሚል ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ መደረጋቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ አመለከተ።
ወያኔ ኢህአዴግ ያለጠንካራ ተቃዋሚ በሚሮጥበት የአዲስ አበባ እና የክልል ምርጫ በአዲስ አበባ ሴቶች ሊግ አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ እና ማስፈራሪያ ሲያደርግ መቆየቱን የገለጠው ዘጋቢያችን ቃለ መሃላ ለመፈጸም የወቱት ሴቶች በነፍስ ወከፍ ኮፍያ እና ቲሸርት የታደላቸው ሲሆን አንዳንዶቸች አበል እንደተከፈላቸውም ታውቋል። በተለያዩ መኪኖች ላይ ቅስቀሳ ያደርጉ የነበሩ ሴቶች ህዝብ የሰለቸውን የመለስ ዜናዊን ፎቶ የያዙ ቲሽርቶችን በመልበስ እንዲሁም ፎቶግራፋቸውን በመያዝ እንደግፋለን ሲሉ መዋላቸው ታውቋል።
ይህን ቃለ መሃላ ከፈጸሙት ሴቶች ውስጥ አንዷን አዛውንት ያናገረው ዘጋቢያችን እንደገለጠው፣ ሁሉም ቃለ መሃላ ፈጻሚ ሴቶች ሙሉ በሙሉ በጥቅም ተገዝተው እንጂ ከልብ የወያኔ አገዛዝ ድጋፍ ኖሯቸው እንዳልሆነ  ማንም ኢትዮጵያዊ ያውቃል ማለታቸውን ገልጧል።

በብሄር ከፍፈሎ መግዛት የዛገ ፖሊሲ ነዉ!

በሀገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች የመዘዋወር፣ ንብረትን የማፍራት፣ የመኖር፣ የመናገር፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብቶች የሚወሰነው በጥቂት የህወሃትና ጀሌ ባለስልጣኖች መልካም ፈቃድ እንጅ በመሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ድንጋጌ አይደለም።
በሩዋንዳ የተፈጸመው የሰውልጅን ዘር የማጥፋት ድርጊት፣ በሀገራችንም ኢትዮጵያ በህወሃት ኢህአዴግ አማካኝነት እየታየ ነው። ዜጎች በማንነነታቸው ከየት አካባቢ/ ብሄር/ ዘር ማንዘር ነው የመጣኸው/ሽው? እዚህ ለመኖር፣ ለመስራት፣ ንብረት ለማፍራትና ለመሳሰሉት የመኖሪያ ፈቃድ አለህ/ሽ ወይ? በሚል ብሄርን ከፋፍሎ መለያ በመስጠት ተከባብሮ የኖረን ህዝብ በትውልድ ሀገሩ እርስ በርሱ ለማጋጨት እየተደረገ ያለው የዛገ የፖለቲካ ፖሊሲ የሀገራችንን ህልውና እየተፈታተነ ነው።
በብሔር ብሔረሰብ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ዘርን በማጥፋት ፖለቲካ የተጠመዱት ወያኔዎች፣ እንደ ሰደድ እሳት በአገራችን ዜጎች ላይ ያላቸውን ጥላቻ ከወዲያ ወዲህ እየሄዱ ያሳዩናል። በተለይም በአማራው የተጀመረው የበቀል ርምጃ ቀጥሎና ተባብሶ የጥፋት በትራቸው የገረፋቸው የኦጋዴን፤ የጋምቤላ፤ የደቡብ ክልል፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የዋልድባ አባቶች የቅርብ ግዜ በደሎች ሳይረሱ ከበደል ላይ በደል፣ ከጩኸት ላይ ጩኸት እየጨመረ በማን አለብኝነት የጀመረውን ዘርን የማጥፋት አባዜ ቀጥሎበታል።
የዜጎችን ሰዋዊ መብት ወያኔ በጠበንጃ ሃይል ጉልበት በመተማመን ንብረትን ቀምቶ፤ ነፍሰጡርንና አራስን አፈናቅሎ፣ ህጻናትን ሜዳ ላይ በትኖ ማባረር፣ የድብደባና የግድያ ወንጀሎች በአማራው ሕዝብ ላይ መፈጸሙ አዲስ ያልሆነና ከበፊቱም የነበረውን የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ የዛገ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረጉት እንደሆነ ያሳየ ምልክት ነው። ይህ ዓይነቱ ዘግናኝ ወንጀል በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች በተለይም በኦጋዴን፣ በአኝዋክ፣ በኦሮሞ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በሙርሲ እና በሌሎችም የማህበረሰባችን ክፍል ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጽሟል። አሁንም እየተፈጸመ ነው።
ህወሃት/ኢህአዴግ ይህንን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመበት ዋናው ምክንያት የአንድን ዘር የፓለቲካ፣ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነቱን ለማስጠበቅ ስለሆነ፤ ለዚህ እኩይ ዓላማው መሳካት እንቅፋት ናቸው ብሎ በሚገምታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ወደፊትም ተመሳሳይ እርምጃ ከመፈጸም እንደማይቆጠብ እየነገረን ነው።
ይሁን እንጅ ወያኔና አበሮቹ ይህ ዘርን የማጥራት (Ethinc Cleansing) ወንጀል ሲፈጽሙ በየትኛውም ግዜና ዘመን ከተጠያቂነት ወይም በወንጀል ከመፈለግ እንደማይድኑ የተረዱ አልመሰለንም።
የወያኔን የዘር ማጥራት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቃወመዉ እና በተለይም አማራዉ ከትውልድ ቀዪው በግዳጅ ተባሮ ለጎዳና ተዳዳሪነት ሲዳረግ የተመለከተ የአካባቢዉ ነዋሪ ህዝብ በፍጹም ወያኔን ያልደገፈና ያልተባበረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ማፈናቀሉን ተቃዉሞ ተፈናቃዮቹን እንባ እያፈሰሰ፣ ለስደት ጉዟቸው ይሆን ዘንድ ራሱ አማራው አርሶና ቆፍሮ እሸት ካፈራበት ማእድ ወይም የዛሬ የበይ ተመልካች ከሆነበት ማሳ ስንቅ እየቋጠረ ነበር የሸኛቸው።
ለብዙ አመታት አብረዉ ከመኖራቸዉ የተነሳ የአብሮ መኖር ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የገነቡና በጋብቻና በማህበራዊ ኑሮ የተሳሰሩ ዜጎች በወያኔ ፖሊሲ ምክንያት ሳይፈልጉ ሲለያዩ ማየት ምን ያህል አሳዛኝ መሆንን የኢትዮጵያ ህዝብ ይረዳል።
በሌሎች አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የስደት ሀገር የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት በፍርድ ቤት እና በተለያዩ ሚዲያዎች የመኖር መብታቸው ይከበር ዘንድ ሲከራከሩ፤ እኒህ ምስኪን የሀገራችን ዜጎች ግን በትውልድ ሀገራቸው፣ መንደራቸው የመኖሪያ ፈቃድ ተነፍጓቸው፣ ይህንንም እንዳይጠይቁ ሆነው ይባረራሉ።
ታዲያ ይህንና ሌሎች በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደሎች በጋራ ሆነን ለመታገል እንዲሁም ለአለም ድምጻችን ለማሰማት ኢትዮጵያዉያን ለብዙ ግዜ በትላልቆቹ የአገራችን ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አቅቶን ብዙ ዘመን ቆይተናል:: አሁን ግን ሌላ ቢቀር ከምን ግዜም በተሻለ ሁኔታ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በኢትዮጵያ አንድነትና በዚህ አንድነት ዉስጥ መመስረት ሳለለበት የዲሞክረሲ ስርአት የጋራ አመካከት መጥቷል።
ይህንን ኢትዮጵያዊ አንድነት የጋራ ትግልና የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት የማስጠበቅ የነጻነት ትግልን ትብብር እውን እንዲሆን ባለፈው ግዜ በከማል ገልቹ የሚመራዉ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር  ከሁለት አመት በፊት የወሰደዉ የአቋም ለዉጥ እና በቅርቡ ደግሞ በኦነግ ታሪክ ዉስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸዉ ሰዎች የወሰዱት ተመሳሳይ አቋም የሚያሳየዉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን በብሄር ከፋፍለህ ቅጣዉ ፖሊሲ ከኢትዮጵያ መወገድ እንዳለበት እና በሁሉም ወገናችን የሚደርሰው በደል ሰቆቃና ስደት የሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ መሆኑንና በጋራ ሆነን የዛገንየወያኔን የዘር ማጥራት ፖሊሲ የምናስቆበት፣ ለአንዴ ለመጨረሻ ግዜ ታግለን የምናስወግድበት ሰአት ላይ ነን።
በተጨማሪ ወያኔ አገራችንን በብሄር መነጽር ብቻ የሚመለከትበትን መንገድና የሚሸርበዉ ሴራ በብሄር የተደራጁ ድርጅቶችንም እያንገሸገሻቸዉ መምጣቱን፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ወያኔን የማስወገድ እና ኢትዮጵያን የማዳን የትግል ደወል ጥሪ ላይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።
ስለሆነም ግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ነጻነት ንቅናቄ በህዝባችን እየደረሰ ያለውን መፈናቀልና እልቂት ለማስቆም የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል። የዲሞክራሲ ሃይላት ድርጅቶችም ሆነ የሀገራችን ወጣቶች፤ የአማራውና የተቀረው ህዝባችን ጮኸትና ዋይታ በደልና ሰቆቃ በሁሉም የሀገራችን ህዝቦች እየደረሰ ያለ ጥቃት ነውና ለጥሪያቸው የማያዳግም መልስ ለመስጠት ትግሉን  ትቀላቀሉ ዘንድ ጥሪያችን ነው

ወደ ቅሊንጦ እስርቤት ያመሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እስረኞችን እንዳይጠይቁ ተከለከሉ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ሙላት ጣሰው እና አቶ ዳንኤል ተፈራ ሚያዚያ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከከተማ ውጭ ወደሚገኘውና መንገዱ እጅግ አስቸጋሪ ወደ ሆነው ቅሊንጦ እስርቤት እስረኞችን ለመጠየቅ ቢሄዱም ተፈትሸውና መታወቂያ አስይዘው ወደ ውስጥ ገብተው ለ45 ደቂቃ የሚሆን እንዲጠብቁ ተስፋ ከተሰጣቸው በሁዋላ ሃላፊው የሉም ለስብሰባ ስለወጡ ስልክ አያነሱም በሚል ተራ ሰበብ እንዳይገናኙ መደረጋቸውን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አስታውቋል፡፡ Read more from

የመን ውስጥ ምላሱን ተቆረጠውን ሀፊዝ ጨምሮ 25 ኢትዮጵያዊያን ሆስፒታል ገብተዋል


ዮርዳኖስን መኪና ላይ አስረው መሬት ለመሬት ጎተቷት፣ (ሚሚ) ተደፈረች…ቃለ ምልልስ አለኝ፡፡
በግሩም ተ/ሀይማኖት
የመን ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው በደል ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷዋል፡፡ በጅቡቲ አድርገው ቀይ ባህርን ተሻግረው ወደ የመን የሚገቡትን ኢትዮጵያዊያንን በማገት 1000 እና 1500 የሳዑዲ አረቢያ ሪያል እና ከዛም በላይ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲያስልኩ የሚያደርጉ አፋኞች መኖራችን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መግለጼ ይታወሳል፡፡ እነዚህ አፋኞች ያገቱት ሰውን ለማስለቀቅ ገንዘብ የሚልክለት ከሌለ ከተራ ድብደባ እስከ መግደል የደረሰ ቅጣት ይፈጽማሉ፡፡ አይን ማጥፋት፣ ብልት መቁረጥ፣ በእሳት ማቃጠል፣ በህወይት እያሉ መቅበር፣ መድፈር…የመሳሰሉትን ይከውናሉ፡፡ እነዚህን አፋኞች ካገቷቸው ውስጥ 25 ኢትዮጵያዊያን ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገቡ ሲል የመረጃ ምንጬ ገልጾልኛል፡፡ Read more in

ዜጎችን ከስፍራቸው ማፈናቀል አንዱ የኢህአዲግ ማናለብኝ ህገዎጥ ተግባር ነው

ከሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበራት የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት፣ ዜጎች በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት የመንቀሳቀስ፣ የመኖር ፣ የመነገድ ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ነገር ግን ገዢውANDINET NORTH AMERICA ASSOCIATION OF SUPPORT ORGANIZATIONS (ANAASO) ፓርቲ ይሄን የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት በመጣስ በተለያዩ ቦታዎች በዜጎች ላይ የሚያደርሰው ግፍና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነዉ።
በሰለጠነው አለም፣ ዜጎች ከመኖሪያ ስፍራቸው የሚፈናቀሉት፣ የሚኖሩበት አካባቢ ተፈጥሮ ባስከተለው ቀውስ የተጠቃ ወይም የሚጠቃ ከሆነ ነዉ። በአገራችን ኢትዮጵያ እያየን ያለነዉ ግን ኢትዮጵያውያን የተለየ ቋንቋ በመናገራቸው፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ አባል በመሆናቸው በአገራቸው እንደ ባእድ ተቆጥረዉ፣ ነፍጥ በጨበጡ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት ና አገልጋዮቻቸው በኃይል ሲፈናቀሉ ነዉ።
ከጥቂት ወራት በፊት ከደቡብ ክልል በግፍ ተባረው አዲስ አበባ፣ ሰሞኑን ደግሞ ከቤነሻንጉል ጉሙዝ ተባረዉ መተከል እና ፍኖተ ሰላም እንዲሰፍሩ የተደረጉ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ ወገኖቻችንን እንደምሳሌ መጥቀሱ ይበቃል። ከቤኔሻንጉል በአስቸኳይ እንዲባረሩ የተደረጉት ወገኖቻችን ፣ በአውቶብስ እንደ እቃ ታጭቀው፣ ክብራቸው ተገፎ የተባረሩ ሲሆን፣ አንዱ አውቶብስ ከአቅም በላይ ሰው በመጫኑ ምክንያት አደጋ ደርሶ፣ ከአምሳ ስድስት በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሞተዋል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት አሰቃቂ የዘር ማጥራት ወንጀል በኢትዮጵያውያን ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ነው።
ሕወሃት/ኢሕአዴግ ፣ በርካታ የአገራችን ድንግል መሬቶችን ለሕንዶች፣ ለአረቦችና ለቻይናዎች እየሰጠ፤ ከነዚህ አገራት የመጡ ዜጎች በአገራችዉ ያላገኙትን የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ እያደረገ፣ ለነዚህ ለዉጭ አገር ዜጎች ቀይ ምንጣፍ እያነጠፈ፣ ኢትዮጵያዉያንን ግን ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉ፣ ማዋረዱ፣ ማሰሩና መግደሉ፤ የዚህን አገዛዝ ምንነት በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።
በቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች የሚኖረው ሕዝባችን ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች ከሚናገሩ፣ ለዘመናት ተፋቅረው፣ ተዋልደው፣ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ከኖሩ በርካታ ብሄር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ነው። ወላይታው በሲዳማው ላይ፣ ሲዳማው በኦሮሞው ላይ፣ ኦሮሞው በጉሙዙ ላይ፣ ጉሙዙ በአማራው ላይ፣ አማራው በትግሬው ላይ፣ ትግሬው በአፋሩ ላይ፣ አፋሩ በኢሳው ላይ …..ችግር የለውም። ኖሮትም አያውቅም። ገዥዎቻችን ግን እየነጣጠሉ ሲመቱን ኖረዋል፡፡ በመሆኑም በደቡብና በቤነሻንጉል የተከሰተዉ አሳዛኝ የዘር ማጥራት ወንጀል በአገዛዙ የተፈጸመ እንጂ በአካባቢዉ ሕዝብ የተፈጸመ አይደለም። ለዚህም ሕወሃት/ኢሕአዴግ እና አሁን ያሉት አመራሮች ሙሉ ተጠያቂ እንደሆኑ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
ከዚህ ዘረኛና እኩይ ተግባራቸው በአስቸኳይ ተቆጥበው፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ስፍራቸዉ እንዲመለሱ፣ ለደረሰባቸው ግፍም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲሰጣቸውና ለዚህም ተጠያቂ የሆኑ የወረዳ፣ የክልል እንዲሁም የፌደራል ባለስልጣናት በአስቸኳይ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እናሳስባለን።
በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት ይሄን መግለጫ ስናወጣ፣ በርካታ የፖለቲካና የሲቪክ ማህበራት ከኛ በፊት ተመሳሳይ መግለጫ እንዳወጡ ማስታወስ እንፈልጋለን። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀን መረዳት ያለብን መሰረታዊ ሃቅ አለ። ይህ ዓይነቱ ግፍ፣ መግለጫ በማውጣት ብቻ መፍትሄ እንደማያገኝ መረዳት አለብን። ከመግለጫ ማውጣት ባሻገር፣ ዘለቈታዊ ዉጤት ሊያመጣ የሚችል የተቀነባበረ ትግል መጧጧፍ ይኖርበታል።
በዚህ ረገድ፣ ቀዳሚዉ ሥራ ዲሞክራሲያዊ ትግሉን ማስተባበርና ኢትዮጵያዉያንን በአንድ ቡድን ማሰባሰብ በመሆኑ፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምንገኝ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ያለንን ልዩነቶች አቻችለን፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባትና የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ቆርጠን በአስቸኳይ መነሳት አለብን እንላለን። የሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበራት፣ ለዲሞክራሲያዊ ትግሉ የድርሻቸውን ሃላፊነት ለመወጣት፣ ከዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንንም በዚህ አጋጣሚ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ነጻነት የትግል ውጤት ነው
የትም ቦታ የተፈጸመ የፍትህ መጓደል በሁሉም ቦታ ፍትህ ላይ የተቃጣ አደጋ ነው! (ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር)
Injustice anywhere is a threat to justice everywhere! (Martin Luther King Jr.)